የተለያዩ የጥበብ ባለሙያዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ባዝሊካ ‘ነጭ ምሽት’ ተብሎ በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ መሳተፋቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በቫቲካን የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቀድሞውንም የነበረውን አስደናቂ ውበትን በዚህ ዝግጅት ይበልጥ ለማጉላት በምንም መልኩ ቀላል ሥራ እንዳልነበረ አዘጋጆቹ የገለጹ ሲሆን፥ ሆኖም የቫቲካን የባህል እና የትምህርት ጽህፈት ቤት የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. እሁድ ምሽት አርቲስቶችን እና የባህል ባለሙያዎችን ወደ ተቀደሰ እና ንፁህ የማሰላሰያ ቦታ የመራ ጥበባዊ እና መንፈሳዊ ጉዞ በማዘጋጀት ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ መወጣቱን ገልጸዋል።
ብዙ ስሜት የነበረው መንፈሳዊ ጉዞ
ብፁዕ ካርዲናል ሆሴ ቶለንቲኖ የጥበብ ባለሙያዎች ኢዮቤልዩ እና የባህል ዓለምን አስመልክቶ በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለዕለቱ ባዘጋጁት የስብከት ጽሁፍ ላይ ‘የጥበብ ባለሙያዎች ሀላፊነት ውበትን ማጉላት ነው’ በማለት የገለጹትን አባባል ያስታወሱ ሲሆን፥ የቲያትር ልምዱን ተጠቅሞ በተቀደሰው ሕንፃ ውስጥ የነጩ ምሽት ትርኢትን ያዘጋጀው የሥነ ጥበብ ዳይሬክተር የሆነው አንድሪያ ቺዮዲም ይሄንን ሀሳብ እንደሚጋራው ተገልጿል።
በስፍራው የተገኙት መንፈሳዊ ነጋዲያን በባዚሊካው ቅጥር ጊቢ ውስጥ ‘የቅዱስ ጴጥሮስ ትልቁ ደወል’ በሚል ርዕስ በአርቲስት ቢል ፎንታና በተዘጋጀ ሙዚቃ በመታጀብ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፥ ከአቀባበል ሥነ ስርዓቱ በኋላ ጎብኚዎቹ አመሻሹ ላይ ወደ ባዚሊካው መግባታቸው ታውቋል።
መርሃግብሩ በተለያዩ ታዋቂ ሙዚቀኞች በተቀነባበሩ ሙዚቃዎች ደምቆ የነበረ ሲሆን፥ ከአቅራቢዎቹ ውስጥ አንዱ የሆነው ጃኮፖ ዲ ቶኖ ይህንን ትእይንት አስመልክቶ እንደተናገረው “ይህ የማይታሰብ እና የማይረሳ ተሞክሮ ነበር” በማለት ከገለጸ በኋላ፣ “ለእይታ እና ለጆሮ በሚስማማ መልኩ እያንዳንዷን ትንሿ ሙዚቃ ከአካባቢው ጋር ለማዋሃድ ተሞክሯል” ብሏል።
ኮንሰርቱ ከዋናው የድምፅ ምንጭ ከሆነው ሙዚቃ መሳሪያው በቅርብ ርቀት ላይ ለቆሙ ሰዎች እንኳን ምቹ እንደነበር የገለጸው ዲ ቶኖ “ውበት እንደሚያድነን በእውነት አምናለሁ፣ ይህም የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት ኃይል ይሆነናል” በማለት ገልጿል።
ጥበብ እና መጽናኛ
ከዚህም ባለፈ ተሳታፊዎቹ ጥልቅ ስሜት ውስጥ በመሆን በጋራ የጸለዩ ሲሆን፥ መርሃ ግብሩ አልቆ ሲወጡም `በመውጫው በር ላይ በሚገኘው እና ዳግመኛ እንድንወለድ የሚያስችለን የሚስጢር ጥምቀት መጠመቂያ ስፍራ በኩል አድርገው ማለፋቸው እና በመጨረሻም ወደ ሮም በሚወስደው ሰፊው በር በኩል መውጣታቸው ተነግሯል።
የ ‘ነጩ ምሽት’ ፕሮግራምን በበላይነት ያዘጋጀው ቺዮዲ እንደተናገረው “ምናልባት ይህ ጉዞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱም እንደገለጹት ጥበብ ውበትን መልሶ ለማግኘት እና በሆነ መልኩ በዚህ አስቸጋሪ ታሪካዊ ወቅት መጽናኛ እንደሚሆነን አስባለው” ሲል የተናገረ ሲሆን፥ በማከልም አርት ወይም ሥነ ጥበብ መሰጠትን እና ተሳትፎን እንደሚጠይቅ በመግለጽ “እኛ የምንኖረው ብዙ አርቲስቶች እራሳቸውን አጉልተው ለማሳየት በሚጥሩበት ጊዜ ላይ ነው፥ ነገር ግን አርቲስት በሥራው አንድ ታሪክ መናገር መቻል አለበት፥ ከዚህም አልፎ በሙያችን የተስፋ ምንጭ መሆን አለብን ብዬ አጥብቄ አምናለሁ” ሲል ቺዮዲ ተናግሯል።
በውበት ውስጥ የሚገኝ ራስን መርሳት
በዝግጅቱ ላይ ከተገኙት በርካታ የጥበብ ሰዎች መካከል ጣሊያናዊቷ ተዋናይ ክላውዲያ ኮል ስትሆን፥ ኮል ስሜታዊ ስለሚያደርገው እና በመርሃ ግብሩ በኩል ዳግም ስለተፈጠረው ውበት በመጥቀስ ይህ ዝግጅት “የእምነት የመጨረሻው መዳረሻ” የሆነውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ የመቃብር ሥፍራ በተወሰነ ደረጃ እንደሚያስታውሳት ገልፃለች።
ከኮል ጋር የነበረችው ተዋናይት ዳንኤላ ፖጊ በበኩሏ በዝግጅቱ ጥልቅ የሆነ ደስታ እንደተሰማት በመግለጽ፥ “የኪነ ጥበብ ዳይሬክተሩ በሰራው ሥራ፣ በዚህ ብርሃን በተሞላው እና ተስፋን አጥብቃችሁ እንድትፈልጉ በሚያደርግ ዝግጅት በጣም ኃይለኛ የሆነ መንፈሳዊ እይታ ውስጥ በመግባት ራሴን አጥቻለሁ፣ ብሎም ራሴን ረስቻለሁ” ካለች በኋላ፥ ዝግጅቱ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲሁም ወደ መንፈስ ቅዱስ የወሰዳት ምሽት እንደሆነ ገልፃለች።
በተጣሉት ላይ ያለው የተስፋ ጭላንጭል
ሌላኛው በዝግጅቱ ላይ የተገኘው ጣሊያናዊው ገጣሚ ጆቫኒ ሮማ እንደተናገረው ዝግጅቱ በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ ለምትገኘው ዓለም ብርሃንን ለማምጣት እንደ ተልእኮ ቢታይ ከዚህም በላይ ትርጉም ይሰጣል” ያለ ሲሆን፥ “ውበት ብዙውን ጊዜ በሚገለጥበት ቦታ ብቻ ሳይሆን በተጣሉት እና በተረሱት ላይም መታየት ይገባዋል” በማለት ሃሳቡን ሰንዝሯል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙ በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ይህንኑ ሃሳብ በማስተጋባት ኪነጥበብ የበለጠ ህብረተሰብን ያሳተፈ እና ለሰላም ግንባታ ላይ እንዴት አስተዋፅዖ ሊያበረክት እንደሚችል ጠቁመዋል።