MAP

ማህበራዊ ሚዲያ ማህበራዊ ሚዲያ  

ቅድስት መንበር በአውሮፓ የሚታየውን ጸረ ሴማዊነትን ለመግታት የዲጂታል ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ አሳሰበች

የአውሮፓ የደህንነት እና ትብብር ተቋም (OSCE) የቅድስት መንበር ተወካይ የሆኑት አባ ዶሜኒኮ በድህረ ገጽ የሚደረጉ የኦንላይን ንግግሮች ላይ የሚታዩ ፀረ ሴማዊነት ያላቸው ይዘቶችን ለማጥፋት የዲጂታል ተጠያቂነት እና ትምህርት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአውሮፓ ውስጥ እየታየ ያለው ፀረ-ሴማዊነት በአይሁድ ማህበረሰቦች ላይ ከፍተኛ ስቃይ ያስከተለ ጥልቅ ታሪካዊ መነሻ ያለው የረጅም ጊዜ ጉዳይ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መንገዶች እየታዩ ያሉትን የጸረ ሴማዊነት ድርጊቶችን ለማስወገድ ትምህርት፣ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ሥርዓት ማስያዝ ቁልፍ የሆኑ ጉዳዮች እንደሆኑ ቅድስት መንበር አሳስባለች።

ትምህርት እና ግንዛቤ ማስጨበጫ
የኖርዲክ ሃገራት ሐዋርያዊ አስተዳደር ፀሐፊ የሆኑት አባ ዶሜኒኮ ቪቶሎ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በአውሮፓ የደህንነት እና ትብብር ተቋም ውስጥ ጸረ ሴማዊነትን አስመልክቶ በተካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

አባ ዶሜኒኮ በንግግራቸው ችግሩን በጥንቃቄ መገምገም እና ለአይሁድ ማህበረሰቦች ያለው አክብሮት በትምህርት ካልዳበረ በቀር በፀረ-ሴማዊነት ላይ ምንም ዓይነት ውጤታማ ለውጥ ሊኖር እንደማይችል የቅድስት መንበርን እምነት እና አቋም በመግለጽ፥ “በተገቢው የትምህርት አካሄድ ብቻ ፀረ ሴማዊነትን እና መድልዎን በብቃት እና በዘላቂነት መዋጋት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ድንቁርና፣ ጭፍን ጥላቻ እና ግትር አመለካከቶች በህብረተሰባችን ውስጥ ፀረ ሴማዊነት እንዲፈጠር አስተዋፅዖ ያደርጋሉ” ያሉት ካህኑ “ትምህርት ህብረተሰባችንን በተለይም ህጻናትና ወጣቶች የሁሉንም ሰው ሰብአዊ ክብር የመጠበቅ የጋራ ሃላፊነትን እንዲገነዘቡ በማድረግ በእነሱ ላይ ጥሩ ሥነ ምግባር ሊገነባ ይችላል” ብለዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተጠያቂነት
አሁን ባለንበት የማህበራዊ ሚዲያ እና የዲጂታል ግንኙነት ዘመን ጸረ ሴማዊ ይዘት ያላቸው ዝግጅቶችን ጨምሮ የጥላቻ ንግግሮች በፍጥነት እና በብዛት በስውር ይሰራጫሉ።

የዲጂታል መድረኮችን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ለመጠቀም ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና መንግስታት ንቁ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ቅድስት መንበር ያሳሰበች ሲሆን፥ “ፀረ-ሴማዊ አገላለጾች አሁን ካለንበት ከዲጂታሉ ዘመን ከረጅም ጊዜያት በፊት የነበረ ሲሆን፥ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት እና የማህበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት መሠረታዊ የአመለካከት ለውጥን አምጥተዋል” ሲሉ አባ ቪቶሎ የጠቆሙ ሲሆን፥ “በእርግጥም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጭ ጸረ-ሴማዊነት ያለው ይዘት ዓለም አቀፍ ታዳሚ እንደሚያገኝ እና ከሌሎቹ ይዘቶች ጎልቶ እንደሚወጣ በማስታወስ፣ በአልጎሪዝም የአሰራር ሥርዓት በኩል ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተባዝቶ ይሰራጫል ብለዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ከዚህም በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለያዩ ይዘቶችን የሚያዘጋጁ ሰዎች ማንነታቸውን መደበቅ እንደሚችሉ በመግለጽ፥ ይህ ሁኔታ አሁን ላይ ደግሞ ፍጹም እውነት በሚመስል እና ሰዎችን ለማሳሳት በሚችል መልኩ የተሳሳተ መረጃን ማመንጨት በሚችለው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ በኩል በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉን አስታውሰዋል።

አባ ቪቶሎ የሳይበር ጥላቻ እና በሰው ሰራሽ አስተሎት የሚመነጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን መዋጋት የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ለበለጠ ጥቅም የሚተጉትን ሁሉንም ግለሰቦች ተሳትፎ እንደሚጠይቅ በማሳሰብ፥ “ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ከመጉዳት ይልቅ ክብርን ለማስጠበቅ፣ ከጥቃት ይልቅ ሰላምን ለማስፈን እንዲውል፣ ህብረተሰቡ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ንቁ እርምጃዎችን በመውሰድ የሰውን ልጅ ክብር ለመጠበቅ እና መልካም እሴቶችን በማሳደግ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ተግተው መስራት አለባቸው” ብለዋል።

ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት
የቅድስት መንበር ተወካይ የሆኑት አባ ቪቶሎ በመጨረሻም የሰው ልጆች እንደ ግዑዙ ዓለም ሁሉ በዘመን አመጣሹ የድህረ ገጽ ግንኙነት ቴክኖሎጂዎችም ላይ ተመሳሳይ መብቶች እና ጥበቃዎች ሊደረግላቸው እንደሚገባ በማስታወስ፥ “ሰዎች ከአውታረ መረቡ ዓለም ውጭ ያላቸው ተመሳሳይ መብቶች በአውታረ መረቡም ላይ የሚጠበቁ ከሆነ፣ ከአውታረ መረብ ውጭ ያላቸው ተዛማጅ ተግባራት እና ኃላፊነቶች እንዲሁ በአውታረ መረብ ቀጥታ ግንኙነት ላይም ሊጠየቁ ይገባል” በማለት አጠቃለዋል።

ለሁለት ቀናት የተካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ በአውሮፓ የደህንነት እና ትብብር ተቋም እንዲሁም 57ቱ አባል ሀገራት በአይሁድ ህዝብ እና ተቋማት ላይ የሚደርሰውን አለመቻቻል እና አድልዎ ለመዋጋት በወሰዱት ሁለንተናዊ አቀራረብ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።
 

13 Feb 2025, 13:45