ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ‘የሰላም ቁርጠኝነቱ ሊኖረን ይገባል’ አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ለሰላም ያለን ቁርጠኝነት “አሁን በምንኖርበት ውስብስብ ዓለም አውድ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነትን በመፈለግ እና ሲቪሎችን ለመጠበቅ እርምጃዎችን በመውሰድ ብቻ የተገደበ አይደለም” ሲሉ በቫቲካን የውጪ አገራት ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሃፊ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር አርብ ዕለት የተናገሩ ሲሆን፥ ከዚህም ይልቅ ግጭት ከመፈንዳቱ በፊት እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል ማመን፣ የግጭት እና የኢሰብአዊነት አስተሳሰቦችን በመተው፣ በየቦታው አብሮነትንና ወንድማማችነትን ለመገንባት መጣር፣ የአዕምሮ ጥንካሬ እና የጠላትነት መንፈስን ለማሸነፍ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ እና ከህዝብ ጋር ለእውነተኛ እና ዘላቂ ዕርቅ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ሊቀጳጳስ ጋላገር ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የጦር ሃይሎች፣ የፖሊስ እና የጸጥታ አስከባሪ አካላት ኢዮቤልዩ አካል ሆኖ ሮም በሚገኘው የቅዱስ ሉዊስ ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል “ሰላምን ለማረጋገጥ ወታደራዊ ሃይል ያለው ድርሻ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቫቲካን የአትክልት ስፍራ ከእስራኤል እና ከፍልስጤም ፕሬዝዳንቶች ጋር ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ባደረጉት ሥነ-ሥርዓት ላይ ሰላምን ለማምጣት ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ የተናገሩትን ፍሬ ሃሳብ በማስተጋባት የንግግራቸው ርዕስ በማድረግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በወታደራዊው እውነታ ላይ እየታየ ያለውን ለውጥ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር “የዛሬው ሰላም እንደ ተራ ነገር ሊቆጠር አይገባም” ካሉ በኋላ፥ “የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ተቋማቱ በሃገራት መካከል መተማመንን ለማስቀጠል ያላቸውን ብቃት በተመለከተ ጥርጣሬ እየጨመረ መጥቷል በማለት አሳስበዋል።
የዘመናዊ ግጭቶች ተፈጥሮ
በተለየ ሁኔታ በዘመናዊ ግጭቶች ተፈጥሮ ላይ ያተኮሩት የቫቲካን የመንግስታት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ዋና ፀሃፊ የሆኑት ሊቀጳጳስ ጋላገር “በአሁኑ ጊዜ ጦርነት በኃይል አጠቃቀም ላይ ብቻ የተገደበ ስላልሆነ ሰላምን በመፈለግ ብቻ ግጭት እንዳይፈጠር ለማድረግ መጣር ቅዠት ይሆናል” ሲሉ አስታውሰዋል።
ብጹእነታቸው አብዛኛውን ጊዜ ዘመናዊ ግጭቶች ሁለገብ ስለሆኑ ደህንነትን ለማስጠበቅ ሁሉን አቀፍ የሆነ አቀራረብ እንደሚያስፈልግ በማስታወስ፥ “የምግብ፣ የአካባቢ፣ የጤና እና የኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ከግምት ውስጥ መግባት አለባቸው” ብለዋል።
“በሌላ አነጋገር ሰላም በፍትህና በበጎ አድራጎት ላይ የተመሰረተ ሥርዓት መገንባትን ይጠይቃል” ያሉት ሊቀጳጳስ ጋላገር፥ ይህም የአብሮነት፣ የጋራ ቤታችንን የመጠበቅ እና የጋራ ጥቅምን የማስከበር ውጤት ነው በማለት አክለዋል።
ሰላምን ለማምጣት ሁለገብ ከሆነ አጠቃላይ እይታ በተጨማሪ የግጭቶቹ ዓይነት በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚለያዩ የግጭቶችን መንስኤ እና ዓይነት ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ እንደሆነ ያብራሩት ሊቀጳጳሱ፥ “ከቀጥታ እና ተለምዷዊ ጦርነቶች ባሻገር፣ ዛሬ የውክልና ጦርነቶች፣ የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ የተረሱ እና የተራዘሙ ግጭቶች እና ጦርነቶች ወደ አገር አቋራጭ ግጭት እየተለወጡ መሆኑን እያየን ነው” ሲሉም አጽንኦት በመስጠት ተናግረዋል።
የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ግጭቶች
ሦስተኛው የዘመናችን ግጭቶች ገጽታ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች አጠቃቀም ሲሆን ይህም በዓለም ዙሪያ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የጦር መሳሪያዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆኑ ይነገራል። በተለይም ብዙ ሀገራት የጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ባለቤት ሲሆኑ ከዚህም በተጨማሪ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይንም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ይጠቀማሉ። የእነዚህ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች እና ስርዓቶች አጠቃቀም ‘ከባድ የስነምግባር ስጋቶችን ያስነሳል’ ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ በቅርቡ ‘አንቲኳ ኢት ኖቫ’ (Antiqua et Nova) በሚል የወጣው የቅድስት መንበር የእምነት፣ ባህል እና ትምህርት አስተምህሮ ጽ/ቤት ማስታወሻ ሰነድ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በሰብአዊ አስተውሎት መካከል ስላለው ግንኙነት በማስታወስ “ገዳይ የሆኑ ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ የጦር መሳሪያ ስርዓቶች ጦርነትን የበለጠ ‘አስገዳጅ ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር እንዳሉት፣ እንዲህ ዓይነቱን አጥፊ ኃይል ከቁጥጥር ውጪ ማድረግ በርካታ ንጹሐን ዜጎችን ሊጎዳ እንደሚችል በመግለጽ፥ “በጣም ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ፣ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል የሚደረግ ውይይት እና በሃገራት መካከል መተማመን ለመፍጠር በአስቸኳይ በመስራት ከዓለም አቀፋዊ ጦርነት ነፃ ወደሆነ ዓለም በቆራጥነት እንድንጓዝ የሚያስችለንን ሕጎችን ለማውጣት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል።
ደህንነትን ለማስጠበቅ አዲስ አቀራረብ ያስፈልጋል
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በመጨረሻም በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እንደተገለጸው በደኅንነት ጉዳይ ላይ ‘ፍጹም አዲስ በሆነ መንፈስ’ የአዲስ አቀራረብ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን፥ ይህ አካሄድ በዋነኛነት ሁከት አልባ መሆን እንዳለበት በመግለጽ፥ ዓለም አቀፍ አለመግባባቶችን ለመፍታት ጦርነትን እንደ አስተማማኝ መንገድ መጠቀምን በማቆም፥ በዘመናችን ጦርነትን ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረቶች ማበረታታት እንደሚገባ አብራርተዋል።
የቫቲካን የመንግስታት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ዋና ፀሃፊ የሆኑት ሊቀጳጳስ ጋላገር በመካከለኛው ዘመንም ቢሆን ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜም ሁከት የሌለበት ዓለም እንዲፈጠር ጠንካራ ተሟጋቾች እንደነበራት በማስታወስ፥ የወቅቱ ሊቃነ ጳጳሳትም ማንኛውም ጦርነቶችን፣ ብሎም በቅዱስ አውግስጢኖስ እና በቅዱስ ቶማስ የተገለጹ የሞራል ማዕቀፎች ያሏቸውን ‘ፍትሐዊ ጦርነት’ ጽንሰ-ሐሳብ ባሻገር ያሉትንም ጭምር በዘመናቸው አጥብቀው አውግዘዋል ብለዋል።
የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግን ማክበር ያስፈልጋል
በሁለተኛ ደረጃ፣ ይህ ጦርነትን በተመለከተ የ“ፍፁም አዲስ መንፈስ” ጽንሰ ሃሳብ በጦርነት ውስጥ የሰውን ልጅ ክብር እና አንድነት ለመጠበቅ የታለመውን እና “ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ” ተብሎ የሚታወቀውን የህግ ማዕቀፍ መከበራቸውን በጥልቀት መመርመርን እንደሚጠይቅ የገለጹ ሲሆን፥ የግጭቱ አይነት ምንም ይሁን ምን የሰብአዊነት ህግ በጦርነት መካከል ተገቢውን ቦታ እንዲይዝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፥ የሲቪሉ ማህበረሰብም ሆነ ወታደራዊው አካል በሕዝብ ኅሊና በሚመራው የሰብአዊ መርሆች ሕግ ሊጠበቁ ይገባል ሲሉ በአጽንዖት ከገለጹ በኋላ፥ ከቅርብ ወራት ወዲህ በተለያዩ ሁኔታዎች እና ምክንያት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕጎች ችላ መባላቸውን፣ አንዳንዴም ሆን ተብሎ በሚመስል ሁኔታ መዘንጋታቸውን በቁጭት ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጭካኔ ድርጊቶች የመበራከታቸው ምክንያት በተለያዩ የግጭት ቀጣናዎች የሚስተዋሉ ጥቃቶችን ቀላል የማድረግ አዝማሚያ መሆኑን ጠቁመው ‘የሰብአዊ መብት ጥሰትና የጦርነትን አሰራር የሚመለከቱ ህጎች እየተለመዱ በመምጣቱ አልፎ አልፎም ቢሆን በቀላሉ የማይቀር ነው’ ሲሉም አክለው ገልጸው፥ ይሁን እንጂ “ይህ የሰብአዊ የህግ ማዕቀፍ ካልተከበረ እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላምም ሆነ 'ጊዜያዊ' ሰላም ሊኖር አይችልም በማለት አስታውሰዋል።
የሰውን ልጅ ክብር ትርጉም ማወቅ እና ማክበር
የሰብአዊ ህግ መርሆችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በእውነታ ላይ ያሉ ለውጦችን በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግጭቶች ውስብስብነት መገንዘብ እንደሚያስፈልግ የገለጹት የቫቲካን የመንግስታት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ዋና ፀሃፊ የሆኑት ሊቀጳጳስ ጋላገር፥ በእርግጥ እነዚህ ግጭቶች ከእንግዲህ ወዲህ የግድ የመንግስት አካላትን ብቻ ሳይሆን የታጠቁ ቡድኖችን እና የግል ሚሊሻዎችንም ያካትታል ብለዋል።
በአንድ በኩል ይህን የህግ ማዕቀፍ እንዴት እንደሚተገበር ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፥ በሌላ በኩል ግን ይህ ብቻ በቂ እንዳልሆነ እና በግልም ሆነ በቡድን ሁሉንም ተጨባጭ ተግባሮቻችንን መምራት ያለባቸውን መሰረታዊ የስነምግባር መርሆችን አንዳንድ ጊዜ ለመተግበር በጣም አስቸጋሪ በሚያደርጉ የመስክ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ቢሆን እንደገና ማግኘት ይገባናል ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በመጨረሻም “የሰው ልጅ ማኅበረሰብን የሚደግፉና ከፖለቲካዊ፣ ባህላዊ ወይም ሃይማኖታዊ ልዩነቶች ባለፈ አንድ የሚያደርገንን የሰው ልጅ ክብር ትርጉምና ሥነ ምግባራዊ መርሆችን መፈለግና እንደገና ለማግኘት ቁርጠኝነቱ ሊኖረን ይገባል” በማለት አጠቃለዋል።