በተሰበረ ዓለም ውስጥ ቴክኖሎጂ ለጋራ ጥቅም መዋል እንደሚገባ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የበለጸጉ ዲጂታል የሕዝብ መድረኮችን ለመገንባት የተቋቋመው የ “ኒው ፐብሊክ ኔትወርክ” መሥራች አቶ ኤሊ ፓሪሰር ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፥ የግንኙነትን የሞራል ጥራት በማሻሻል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያራምዱ ማኅበራዊ መድረኮችን ማዘጋጀት እንደሚገባ በማሳሰብ፥ ትርጉም ባለው መንገድ በአውታረ መረብ በኩል እንዴት መሥራት እንደሚቻል በማስረዳት ለበጎው አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ማኅበረሰቦችን መገንባት እንደሚገባ ጥሪውን አቅርቧል።
በቫቲካን የመገናኛ ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ከዓለም አቀፍ የገዳማት አስተባባሪዎች ጋር በጥምረት ባዘጋጁት የኢዮቤልዩ ዓመት የመገናኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተገኘው አቶ ኤሊ ፓሪሰር፥ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመገናኛ ባለሞያዎችን የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በማስመልከት አስተያየቱን በመግለጽ፥ በተደጋጋሚ ለሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችም መልስ ሰጥቷል። በጉባኤው ላይ ጳጳሳዊ የመገናኛ ኮሚሽኖች ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የማኅበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤቶች መሪዎች እና ዓለም አቀፍ የገዳማት አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።
በድረ-ገጽ አማካይነት ቴክኖሎጂን እና ዲሞክራሲያዊ ሚዲያን ለመርዳት እንደሚፈልግ የሚናገረው አቶ ኤሊ ፓሪስየር፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2011 ዓ. ም. በርካታ የንግድ ሥራ ስኬቶችን ማስመዝገቡ ታውቋል።ቢል ጌትስ፣ ሰር ቲም በርነርስ-ሊ እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ግዙፍ ኩባንያዎች እና የኢንተርኔት ሊሂቃን በፓሪሰርን የመቆጣጠሪያ ጽንሰ-ሀሳብ ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸው፥ ይህንንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በሚከታተሉት የ “TED” የንግግር መድረክ ላይ የበለጠ ግልፅ ለማድረግ ማገዙ ታውቋል።
ደራሲው ሥራ ፈጣሪው፣ የቴክኖሎጂ እና ዲሞክራሲያዊ ሚዲያን ለማገዝ የተነሳው አቶ ኤሊ ፓሪሰር፥ በአገልግሎት ላይ ያተኮሩ ሌሎች በርካታ ድርጅቶችን እና የዓለማችን ትላልቅ ድርጅትን ለመመሥረት እገዛ ማድረጉ ታውቋል።
በኢዮቤልዩ የመገናኛ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ ያደረገው የምንኖርበት ዓለም የተሰበረ እና አደገኛ ጊዜ በመሆኑ ነው” ያለው አቶ ኤሊ ፓሪሰር፥ በዓለም ላይ ብቻ ሳይሆን በድረ ገጾች አውታረ መረብ ላይ የሚደረግ የእርስ በርስ መገናኛ መንገድ ጭምር እንደሆነ እና የምንግባባበትን የሞራል ጥራት ማስታወስ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን አጋንንትን ሳይሆን መላዕክትን መደገፍ በሚችሉበት መንገድ እንዴት ማዋቀር እንዳለብን ማሰብ በጣም አስፈላጊ መስሎ በማየቱ እንደሆነ አስረድቷል። በጉባኤው ላይ የተገኘውም በውስጣችን ያለውን መጥፎውን ሳይሆን ምርጡን ለሌሎች ለማካፈል የአውታረ መረብ መድረኮችን እንዴት መገንባት እንዳለብን ለመወያየት እንደሆነ ገልጿል።
አሁን ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ለጋራ ጥቅም አለመሥራታቸው ችግር እንደሆነ የገለጸው አቶ ኤሊ ፓሪሰር፥ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች የተገነቡት በሃብት በልጽገው ነገሥታት የሆኑትን እንደ ማርክ ዙከርበርግ እና ኤሎን ማስክ ያሉትን ለማገልገል እንደሆነ ገልጿል። ማኅበረሰብን ለማሰባሰብ መሞከር በጣም ጠቃሚ እንደሆነ የገለጸው አቶ ኤሊ ፓሪሰር፥ ከዚህ በመነሳት ከንግድ መድረኮች አልፈን ሕዝባዊ በጎነትን መቀዳጀት የሚቻልባቸውን መንገዶች ማሰብ መጀመር እንደሚገባ አሳስቧል።
በድረ-ገጽ የአውታረ መረብ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቦችን በገነባንበት መንገድ ጥሩ መነሳሳት እንደተገኘ የሚያስረዳው አቶ ኤሊ ፓሪሰር፥ “በቤተ-መጻሕፍት እና በአብያተ ክርስቲያናት ግንባታ ላይ መዋዕለ ንዋያችን አፍሰናል፣ ሰዎችን ከመሸጥ ይልቅ ሰዎችን ወደ መልካም መንገድ ለማምጣት በሚያስቡ ሁሉም ቦታዎች ላይ ኢንቨስት አድርገናል፤ ያንን የመሰለ ኢንቬስትመንት አሁን በአውታረ መረብ ላይ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል” ሲል አስተያየቱን አካፍሏል።
“New_Public” የተሰኘው ማስታወቂያ አስነጋሪዎችን ብቻ ሳይሆን መላውን ማኅበረሰብ በእውነት የሚያገለግል ዲጂታል የሕዝብ መድረኮችን ለመገንባት የሚያግዝ ቤተ ሙከራ እንደሆነ ገልጾ፥ ከአውስትራሊያ እስከ አውሮፓ እስከ ካናዳ ካሉ የሚዲያ ድርጅቶች ጋር በመሥራት እና እንዲሁም ሰዎች በአካባቢያቸው ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር የሚግባቡበት እና የሚሰባሰቡበት አካባቢያዊ ዲጂታል የሕዝብ መድረኮችን መገንባት መጀመሩን አስረድቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና ለሁሉም የሚሰራ የመገናኛ ሚዲያን መገንባት የሞራል ጠቀሜታ እንዳለው የሚናገሩ ሌሎች ሰዎችንም መስማት በጣም አበረታች እንደነበር አቶ ኤሊ ፓሪሰር፥ ይህም የቴክኖሎጂ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሞራል እና የመንፈስ ጉዳይ እንደሆን ገልጾ፥ ያንን እውነት መስማት እጅግ የሚያነሳሳ እንደ ሆነም አሳረድቷል።