ብፁዕ ካርዲናል ጉጄሮቲ፡ ‘ክርስቲያኖች በሶሪያ የመሪነት ሚና መጫወት አለባቸው’ ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ከደማስቆ ወደ አሌፖ ያለው መንገድ ሶርያ ባለፉት አስር አመታት ያሳለፈችውን ሰማዕትነት ፍንጭ ይሰጣል።
ተጓዦች ከተማዋን ለቀው ሲወጡ በእሳት ቃጠሎ የጠቆረውን የተተው የጦር ሰፈር፣ የተቀደደ እና የተቃጠለ የበሽር አል አሳድ ምስል የያዘ የተለጠፈ ማስታወቂያ፣ በአዲስ ብሄራዊ ባንዲራዎች ተሸፍነው፣ በዋና ጎዳናዎች ላይ በጥይት የታጨቁ የጦር መኪኖች እና የከተማ ዳርቻዎች በሙሉ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።
የሃማ አካባቢ ፋብሪካዎች የተዘጉበት እና ብዙ ፋብሪካዎች የተቃጠሉበት እና የፈረሱበት ሁኔታ ይታያል።
ከጥቂት የተፈናቀሉ ካምፖች በስተቀር የሆምስ ከተማ ዳርቻዎች በበረሃማ መንደሮች የተሞላ ነው። እ.ኤ.አ. በ2023 ዓ.ም በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ውድመት ባጋጠመው ፍርስራሹ ለኢድሊብ ገጠራማ አካባቢም ተመሳሳይ ነው።
በመጨረሻም፣ አልፎ አልፎ በጥቂት የተሰላቹ ሚሊሻዎች ከተያዙት የፍተሻ ኬላዎች በኋላ፣ ህመም እና ስቃይ የተሸከመችው አሌፖ ትገኛለች።
አዲሲቷ ሶሪያ ገና በእርግዝና ላይ ነች
እሁድ እለት ጥር 18/2017 ዓ.ም በቫቲካን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ በበላይነት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት አስተዳዳሪ የሆኑት እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ በአንድ ወቅት በአረቡ ዓለም ሦስተኛዋ ትልቅ የክርስቲያን ከተማ ከ300,000 በላይ የሚሆኑ ከተለያዩ ቤተ እምነቶች የተውጣጡ ክርስቲያኖች የሚኖሩባት ከተማ ደረሱ። ዛሬ ከ30,000 በታች የሆኑ ክርስቲያኖች ብቻ በሥፍራው ቀርተዋል።
በስፍራው በሚገኘው በቅዱስ ፍራንችስኮስ ቤተክርስትያን ውስጥ ለተሰበሰቡት የላቲን ስርዓት ተከታይ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች "አዲሲቷ ሶሪያ አሁንም በእርግዝና ላይ ነች" ሲሉ ተናግሯል። "ነገር ግን ስትወለድ ጥሩ አዋላጅ ያስፈልጋታል፣ እናም ይህ የክርስቲያኖች ተግባር ነው" ብለዋል።
ካርዲናል ጉጄሮቲ በሁሉም ቤተ እምነቶች ያሉ ክርስቲያኖች የሚያጋጥሟቸውን መጠነ ሰፊ ችግሮች እና እርግጠኛ ያልሆኑ ችግሮች እንዳሉ አምነዋል፣ ነገር ግን ፍርሃታቸው ወደ ሽባነት ሊመራ እንደማይገባ አሳስበዋል። የሶሪያ ክርስቲያኖች ከሌሎች ዜጎች ጋር እኩል ሆነው ሚናቸውን ለማግኘት እና አዲስ ሀገር ለመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ የሚያደርጉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው ብለዋል ።
ካርዲናል ጉጄሮቲ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅርበት እና ጸሎት ለሶሪያ ክርስቲያኖች አጋርተዋል። በእሁድ ስብከታቸው “አንድ አካል መሆን ማለት ሁሉም አባላት እኩል ጠቀሜታ አላቸው ማለት ነው። ራስ ወዳድነት ሊኖር አይችልም፣ ክርስቲያን የመሆን ዋናው ነገር ይህ ነው ብለዋል።
የስደተኞች መመለስ
በፍራንችስኮስ ገዳም በቫቲካን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ በበላይነት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት አስተዳዳሪ የሆኑት እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፣ ከጣሊያን አምባሳደር ስቴፋኖ ራቫግናን እና ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ጋር በመገናኘት ቀኑን አጠናቅቀዋል።
ከባለፈው ሕዳር ወር ጀምሮ በአለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት አማካይነት ስደተኞች ወደ ሶሪያ መመለስ ጀምረዋል። እስካሁን በትንሹ 210,000 ስደተኞች ከጎረቤት ሀገራት የተመለሱ ሲሆን በአጠቃላይ ወደ 600,000 የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው መመለስ ችለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ፊሊፖ ግራንዲ “አሁን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሽግግሩን ሂደት ለመደገፍ እና ሀገሪቱን መደበኛ ለማድረግ ጥረቶችን የምያደርግበት እና መፍትሄዎችን የሚወስድበት ጊዜ ነው" ብለዋል።
በቫቲካን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ በበላይነት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት አስተዳዳሪ የሆኑት እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ ከኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ጋር ሰላምታ ተለዋውጠው ህይወትን መልሶ ለመገንባት እና የሶሪያን ህዝብ ተስፋ ለመመለስ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው መነጋገራቸው ተዘግቧል።