MAP

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በኮንጎ ብራዛቪል መስዋዕተ ቅዳሴን ሲያሳርጉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በኮንጎ ብራዛቪል መስዋዕተ ቅዳሴን ሲያሳርጉ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በተፈጥሮ አደጋ ከተጎዳው የኮንጎ ብራዛቪል ሕዝብ ጎን መሆናቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ብራዛቪል በተከታታይ እየደረሱ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ተገንዝበው ለሕዝቡ ያላቸውን አጋርነት መግለጻቸውን በቫቲካን የአገራት ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር አስታወቁ። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ላለፉት ጥቂት ቀናት በኮንጎ ብራዛቪል ቆይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዋና ጸሃፊው ወደ ሥፍራው የተጓዙት የጋራ ኮሚሽኑን የስምምነት ማዕቀፍ ማስፈጸሚያ ሥነ-ሥርዓት ለመሳተፍ እንደ ነበር ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2017 ዓ. ም. የተፈረመው እና ከ 2019 ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለው ስምምነቱ በኮንጎ ብራዛቪል የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ተቋማት ሕጋዊነታቸው ታውቆ ነፃነታቸውን እና ራስ ገዝነታቸውን ለመጠበቅ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።

ወደ አገሪቱ የተደረገ ልዩ ሐዋርያዊ ጉብኝት
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር ወደ ኮንጎ ሪፐብሊክ ያደረጉት ጉዞ መርሃ ግብር በልበ ኢየሱስ ካቴድራል አደባባይ ያቀረቡትን መስዋዕተ ቅዳሴን እና የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች የኢዮቤልዩ በዓልን ያካተተ እንደ ነበር ታውቋል። በበዓሉ ላይ የኮንጎ ብራዛቪል ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቢየንቨኑ ማናሚካ፣ በኮንጎ ብራዛቪል የቅድስት መንበር እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ ዛቪዬር ሄሬራ ኮሮና እና የኮንጎ ብጹዓን ጳጳሳት ተገኝተዋል።

በቫቲካን የአገራት ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ከሀገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ከተገናኙ በኋላ ማክሰኞ ጥር 6/2017 ከዓለም አቀፍ፣ ከግል እና ከሕዝብ ትብብር ሚኒስትር ጋር ተገናኝተዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይወዷቸዋል”
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በመስዋዕተ ቅዳሴው ባሰሙት ስብከት ላይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሰላምታ እና ቡራኬ ካደረሱ በኋላ ቅዱስነታቸው የኮንጎን ሕዝብ ሕይወት በትኩረት እንደሚከታተሉ ገልጸዋል። በመቀጠልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚወዷቸው እና ሕዝቡ ለሰላም እና ለወንድማማችነት ያለውን ተስፋ እና ፍላጎት እንደሚያቁ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሲታወቅ፥ ከዚህ ተግዳሮት አንፃር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአደጋው ከተጎዳው ሕዝብ ጎን መሆናቸውን አብራርተዋል።

የእምነት ምስክሮች
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር የኮንጎ ሕዝቡ ለወንጌል ምስክርነት፣ ፍትሃዊ እና ወንድማማችነት ያለው ማኅበረሰብን ለመገንባት ያደረገውን ጥረት በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የላኩትን ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።

“በአገሪቱ የእምነት ምስክሮች እጥረት የለም” ሲሉ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ በተለይም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1977 ዓ. ም. በሰማዕትነት የተገደሉትን የእግዚአብሔር አገልጋይ የካርዲናል ኤሚል ቢያየንዳ ሕይወት አስታውሰዋል።

በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1973 ዓ. ም. የካርዲናልነት ማዕረግ የተቀበሉት አቡነ ኤሚል ቢያየንዳ የብጽዕና ጥናት የተጀመረው በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጊዜ እንደ ነበር ይታወሳል። የካርዲናል ቢያየንዳ አጽም በብራዛቪል ካቴድራል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ ይህ ሥፍራ የሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጉብኝት መጀመሪያ ቦታ እንደ ነበር ታውቋል።

የኢዮቤልዩ በዓል ለሁሉ ሰው የቀረበ ግብዣ ነው!
በስብከተ ወንጌል ላይ አፅንዖት በመስጠት ጥሪያቸውን ያቀረቡት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ ይህም በተለይም በኢዮቤልዩ ዓመት ጠንክሮ እንዲቀጥ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ ለወጣቶች፥ “ተስፋችሁ እንዳይሰረቅባችሁ” በማለት ያቀረቡትን መልዕክት በማስታወስ፥ ወጣቶች ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ የወደፊ ጊዜን በተስፋ እንዲጠብቁ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

 

14 Jan 2025, 17:07