ሊቀ ጳጳስ ፓሊያ ቤተክርስቲያን በሌላ ሰው ድጋፍ የሚደርገውን ራስ ማጥፋት ትቃወማለች አሉ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ቤተክርስቲያኗ በሌላ ሰው ድጋፍ ራስን ማጥፋትን እና በማይድን ሕመም የተያዙትን ሰዎች ሕልፈት ማቅለል (ዩቲኔዚያ) በፍጹም ትቃወማለች እናም የእያንዳንዱን ሰው በተለይም በጣም ተጋላጭ የሆኑትን በህይወት የመኖር መብት ትጠብቃለች፣ በማይድን ሕመም የተያዙትን ሕልፈት ማቅለል (ዩቲኔዚያ) ሕይወትን በተመለከተ ከባለድርሻ የፖለቲካ ማሕበረሰቦች ጋር ስለጉዳዩ አስፈሪነት እና ኢፍትሃዊነት በመጥቀስ ተባብራ ትሰራለች ብለዋል።
የጳጳሳዊ የሕይወት ከፍተኛ ተቋም ሊቀ ጳጳስ ቪንቼንሶ ፓሊያ የሥነ ምግባር ጉዳዮችን በሚመለከት በLEV (ቫቲካን ማተሚያ ቤት) የታተመው ባለ 88 ገጽ የቃላት መፍቻ “በሕይወት መጨረሻ ላይ ያለው ትንሽ መዝገበ-ቃላት” በሚለው ጥቂት ነጥቦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማይድን ሕመም የተያዙትን ሰዎች ሕልፈት ማቅለል (ዩቲኔዚያ) እና በሌላ ሰው እገዛ ራስን ማጥፋትን እና አስከሬን እስከ ማቃጠል ድረስ ያሉ የህይወት መጨረሻ ክርክሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚዳሥሥ መጽሐፍ ነው።
በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የታተመው በራሪ ወረቀት አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን በቅድስት መንበር “መከፈቻ” ብለው ያዩትን ነገር በማጉላት በቅርብ ጊዜ ትኩረት ተሰጥተውታል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ሊቀ ጳጳስ ፓሊያ ለቫቲካን ዜና በሚቀጥለው ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት፣ እነዚህ ምልክቶች ባለፉት 70 ዓመታት የርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳትና የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይ የተመሠረቱ ናቸው ብለዋል።
ሐሙስ ጥዋት ነሐሴ 02/2016 ዓ.ም ሊቀ ጳጳስ ፓሊያ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤታቸው ውስጥ ተገናኝተው የ‹‹መዝገበ ቃላትን›› ቅጂ አቅርበዋል።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በማይድን ሕመም የተያዙን ሰዎች ሕልፈት ማቅለል (ዩቲኔዚያ) በከፍተኛ ሁኔታ ይቃወማል። የመኖር ተስፋቸው የመነመነ ወይም የተዳከሙ ሰዎች ልዩ እንክብካቤ ይገባቸዋል። ሕመምተኞች ወይም የአካል ጉዳተኞች በተቻለ መጠን እንደ ሌሎች ሁሉ ሕይወታቸውን ይመሩ ዘንድ እርዳታ መግኘት ይኖርባቸዋል። አላማዎቹና የሚጠቀምባቸው ብልሃቶች የቱንም ዓይነት ይሁን ዩቲኔዝያ የታመመን፣ በሞት አፋፍ ላይ ያለንና አካል ጉዳተኛ የሆነውን ሰው ለሕልፈት መዳረግ ነው። ይህ ድርጊት ከስነ-ምግባር አንጻር ተቀባይነት የለውም።
ስለሆነም የሆነ ድርጊት ወይም ጥፋት በራሱ ወይም ይሁን ተብሎ በታሰበ መንገድ ስቃይን ለማስቀረት ሲባል ሞትን የምያስከትል ከሆነ ፍጹም ለሰብአዊው አካል እና ለፈጣሪው ለሕያው አምላክ የተገባውን ክብር የሚጻረር አሰቃቂ ግድያ ነው። በቅንነት የተወሰደ ግድፈት ያለበት እርምጃ ቢሆን ባሕርዩን ስለማይለውጠው ምንጊዜም ቢሆን ግድያው ሊከለከልና ሊቆም የሚገባው ድርጊት ነው (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2276-2277)