ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ "የቤተሰብ ምስክርነት አስፈላጊ ነው" ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዳሜ ጳጉሜ 1/2017 ዓ. ም. ምሽት በተዘጋጀው ፌስቲቫሉ ላይ የምግብ ዝግጅቶች፣ የሥዕል ሥራዎች፣ ልዩ ልዩ አዝናኝ ጨዋታዎች እና የሙዚቃ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን፥ በዕለቱ በርካታ ሕጻናት የተደሰቱበት ዋናው ሥነ-ሥርዓት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን አስተዳደር ሕንጻ ፊት ለፊት ከተሰበሰቡት በመቶዎች ከሚቆጠሩ የቫቲካን ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት የመጡበት አጋጣሚ እንደ ነበር ተገልጿል።
በፌስቲቫሉ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ እናቶች እና አባቶች ከልጆቻቸው ጋር ሆነው በቫቲካን የበጋ ጊዜ መሰብሰቢያ ሥፍራ ተገኝተዋል። የማዕከላዊ መሥሪያ ቤቶች ካኅናትን የሚያስተባብሩት የዶን ቦስኮ ማኅበር ካኅን አባ ፍራንኮ ፎንታና በሰጡት ምልክት መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከቫቲካን ጠቅላይ አስተዳደር ሕንጻ ዋና በር በኩል ከወጡ በኋላ በሥፍራው ለነበሩት በርካታ ቤተሰቦች እና ልጆቻቸው ሰላምታቸውን አቅርበዋል።
“ሁላችንም የእግዚአብሔር ቤተሰብ ነን”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሥፍራው ለነበሩት በሙሉ ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ በፌስቲቫሉ ላይ መገኘታቸው እና ልጆችን ማየታቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፥
“እናት እና አባት ልጆቻቸውን እንደሚወዱ ሁሉ፣ ሁላችን እንደዚህ ስንሰበሰብ፣ እርስ በርሳችን ስንዋደድ፣ ወንድማችን እና የቅርብ ወዳጃችን ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንሆን የእግዚአብሔር ቤተሰብ እንሆናለን” ብለዋል።
በማከልም “በተከፈተ ልብ ይህን ውብ ጊዜን በኅብረት ማሳለፍ እንፈልጋለን” በማለት አጽንዖት ሰጥተው፥ “ቤተሰብ የመሆን እና የአንድነት ደስታን፣ እርስ በርስ የመዋደድ፣ የበዓል፣ በተለይም እግዚአብሔር የሰጠንን የሕይወት እና የቤተሰብ ስጦታ እንጋራለን” ብለዋል።
የቤተሰብ ምስክርነት እና መስዋዕትነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ለወላጆች ባደረጉት ንግግር፥ ዛሬ የቤተሰብ ምስክርነት በዓለማችን ውስጥ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አረጋግጠው፥ ወላጆችን ለምስክርነታቸው፣ በፌስቲቫሉ ላይ ላሳዩት እና ላደረጉት በሙሉ፣ አንድ ላይ ለመኖር ብለው ለሚከፍሉት መስዋዕትነት፣ ይህን መልዕክት ኢየሱስ ክርስቶስ በተወልን መንፈስ ከሌሎች ጋር ለመካፈል ላደረጉት ጥረት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የጋራ ጸሎት እና የስንብት ሥነ-ሥርዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በፌስቲቫሉ ላይ ለነበሩት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ከመስጠታቸው በፊት በኅብረት ሆነው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አድርሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከንግግራቸው በኋላ በፌስቲቫሉ ላይ ከነበሩት ሕጻናት እና ወላጆቻቸው ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል ከቆዩ በኋላ ወደ መኖሪያቸው ከመመለሳቸው በፊት ለፌስቲቫሉ ድምቀት ከሰጡ ተዋንያን ጋር የማስታወሻ ፎቶግራጎችን ተነስተዋል።