MAP

በአፍጋኒስታን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ  በአፍጋኒስታን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ   (ANSA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ አፍጋኒስታን ውስጥ በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጎዱትን በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በምሥራቅ አፍጋኒስታን እሑድ ነሐሴ 25/2017 ዓ. ም. ምሽት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሞቱትን እና የተጎዱትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰው፥ ዘመዶቻቸውን ላጡት በሙሉ አጋርነታቸውን በመግለጽ ለመላው የአፍጋኒስታን ሕዝብ መለኮታዊ ቡራኬን ልከዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በምሥራቅ አፍጋኒስታን እሑድ ነሐሴ 25/2017 ዓ. ም. አመሻሽ ላይ በሬክተር መለኪያ 6.0 በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ 800 ሰዎች መሞታቸው እና በሺዎች የሚቆጠሩ መቆሰላቸው ተነግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የአደጋውን ዜናው እንደሰሙ በአሰቃቂው የተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱት ሰዎች በሙሉ የቴሌግራም መልዕክት በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኩል የላኩ ሲሆን፥ በደረሰው ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአደጋው የሞቱትን፣ የተጎዱትን እና እስካሁን የደረሱበት የማይታወቅ ሰዎችን በሙሉ በጸሎታቸው በማስታወስ የሁሉን ቻይ አምላክ ዕርዳታን ለምነዋል። በተለይም የሚወዷቸውን በሞት ላጡት፣ በነፍስ አድን ዕርዳታ እና በማገገሚያ ዕርዳታ ላይ ከተሳተፉት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እና ለሲቪል ባለስልጣናት ያላቸውን ልባዊ አጋርነት ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቴሌግራም መልዕክታቸው፥ በአስቸጋሪ ወቅት ለመላው አፍጋኒስታን ሕዝብ መጽናናትን እና ጥንካሬን በመመኘት መለኮታዊ ቡራኬያቸው ልከዋል።

በአፍጋኒስታን ውስጥ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ
በአፍጋኒስታን ውስጥ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ

የተከሰተው በትክክል ምንድነው?

ባለፈው እሁድ አመሻሽ ላይ በምሥራቅ አፍጋኒስታን በሬክተር 6.0 በተመዘገበው ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ በትንሹ 812 ሰዎች ሲሞቱ ከ2,800 በላይ መቁሰላቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ሰኞ ዕለት አስታውቀዋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ አደጋ የተከሰተው በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ በአምስት ሰዓት ከአርባ ሰባት ደቂቃ ላይ ሲሆን፥ በጂኦሎጂ መረጃ መሠረት የናንጋርሃር ግዛት ዋና ከተማ ከሆነችው ከጃላላባድ በስተ ሰሜናዊ ምሥራቅ በ27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሥፍራ በጽኑ መጎዳቱ ተነግሯል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደገለጹት፥ ብዙ ነዋሪዎች በፍርስራሹ ውስጥ ተቀብረው እንደሚገኙ የተሰጋ ሲሆን፥ በቀላሉ የማይደረሱ ሩቅ ክልሎችን ለመድረስ ሄሊኮፕተሮች መመደባቸውን ገልጸዋል።

በናንጋርሃር ግዛት ውስጥ 12 ሰዎች እንደሞቱ እና 255 እንደቆሰሉ ባለስልጣናት ያረጋገጡ ሲሆን፥ በላግማን ግዛት ውስጥ 58 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን በኑሪስታን ግዛት ውስጥ ደግሞ አራት ሰዎች መቁሰላቸው ተመዝግቧል።

በአፍጋኒስታን ውስጥ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ
በአፍጋኒስታን ውስጥ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ   (ANSA)

አንድ የመንግሥት ባለስልጣን እንደገለጹት፥ እነዚህ የመጀመሪያ አሃዞች እንደሆኑ እና ግምገማዎች ሲቀጥሉ የተጎጂዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

ወጣ ገባ መሬት የነፍስ አድን ሥራዎችን ቢያወሳስበውም ነገር ግን የዕርዳታ አቅርቦትን እና የፍለጋ ሥራዎችን ለማፋጠን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ ተጎዱት አካባቢዎች መላካቸው ታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” ጉዳቱን ለመገምገም እና የሰብዓዊ ድጋፍን ለማስተባበር ከአፍጋኒስታን ባለስልጣናት ጋር የሚሠሩ የሀገር ውስጥ ቡድኖች እንዳሉት ታውቋል።

 

02 Sep 2025, 17:05