MAP

ር.ሊ.ጳ ሊዮ ቅዱሳን ወደ እግዚአብሔር እንድንመለከት ይጋብዙናል ማለታቸው ተገለጸ

እሁድ እለት ጳጉሜ 02/2017 ዓ.ም ከሰማንያ ሺህ በላይ የሚሆኑ ምዕመናን በወቅቱ በተከናወነው ሥርዓተ አምልኮ ላይ የቅድስና ማዕረግ በተሰጣቸው ቅዱስ ፒየር ጆርጂዮ ፍሬሳቲ እና ቅዱስ ካርሎ አኩቲስ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለመሳተፍ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የነዚህ ሁለት ወጣት ቅዱሳን ምሳሌ ሁላችንን በተለይም ወጣቶች ሕይወታቸው ወደ እግዚአብሔር እንዲያመራ እና የቅድስና፣ የአገልግሎት እና የደስታ ድንቅ ስራዎች እንዲያደርጉ ይጋብዙናል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የፒየር ጆርጂዮ ፍሬሳቲ እና የካርሎ አኩቲስ ማዕረገ ቅድስና ሥነ-ሥርአት ላይ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ያልተለመደ እና ልዩ የሆነ ምስክርነታቸው ለእምነት፣ ተስፋ እና በእግዚአብሔር መታመን ለዘላለማዊ ደስታ እና የጌታን ታላቅ እቅድ በሕይወታቸው ማክበራቸውን የገለጹ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁለቱን ወጣት ጣሊያናውያን ቅዱሳን በበዓሉ መጀመሪያ ላይ በሚያስደንቅ ሁኔታ በሚያምር የበጋው ቀን መጨረሻ እሁድ ቅዱስ መሆናቸውን አውጀዋል።

በስብከታቸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሁለቱም አዲስ ቅዱሳን ልዩ ምስክርነት ላይ አስተንትነዋል። በእለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከመጽሐፈ ጥበብ ተወስዶ የተነበበውን የመጀመሪያው ምንባብ በማስታወስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ልክ እንደ ንጉሥ ሰሎሞን፣ እነዚህ ወጣቶች ሕይወታቸውን እና አለምን የበለጠ ለመረዳት እግዚአብሔርን በታማኝነት ለመከተል የጥበብን ስጦታ ይፈልጉ እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህንንም በማድረጋቸው፣ በአርአያነታቸው፣ በቃላቸው እና በተግባራቸው ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር ለማምጣት እነዚህ አዳዲስ ወጣት ቅዱሳን ስጦታቸውን ተጠቅመዋል ብለዋል።

ራሳችንን ለጌታ መስጠት

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በጦርነት በተጎዱ የዓለም አካባቢዎች በቅድስት ሀገር፣ ዩክሬን እና እንዲሁም በግጭቶች ለሚሰቃዩ አከባቢዎች ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ተማጽነዋል።

በቅዱስ ወንጌል ንባብ ውስጥ፣ ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር እቅድ ተናገረ፣ እሱም በሙሉ ልብ ልንፈፅም እንደሚገባን ኢየሱስ እንደ ሚጋብዘን የገለጹት ቅዱስነታቸው ራሳችንን “ለመሰጠን ሳናቅማማ፣ ከመንፈሱ በምወጣው ዕውቀትና ጥንካሬ” መጓዝ ይኖርብናል ማለታቸው ተገልጿል። ወጣቶች ብዙውን ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ መንታ መንገድ ያጋጥሟቸዋል፣ እናም አስቸጋሪ ምርጫዎችን ማድረግ አለባቸው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እናም የአዚዚውን ቅዱስ ፍራንችስኮስን ምሳሌ በማስታወስ፣ የቅዱሱ ሁላችንም የምናውቀውን አስደናቂ የቅድስና ታሪክ፣ ጌታን ለመከተል ሁሉንም ነገር አውልቆ ጥሎ፣ በድህነት ውስጥ እየኖረ፣ የወንድሞቹን እና የእህቶቹን ፍቅር፣ በተለይም ደካሞችንና ታናናሾቹን ከአባቱ ወርቅ፣ ብር እና ውድ የጨርቅ ልብሶች የበለጠ መርጧል ሲሉ ተናግረዋል።

ለእግዚአብሔር “እሺ” በማለት

በታሪክ ውስጥ ያሉ ብዙ ቅዱሳን ወደ እግዚአብሔር በመመልከት ተመሳሳይ ደፋር ምርጫዎችን አድርገዋል፣ እናም ገና በልጅነታቸው እነዚህ ወጣት ቅዱሳን “እሺ” በማለት ለእግዚአብሔር የታዘዙ መሆናቸውን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የገለጹ ሲሆን “ለራሳቸው ምንም ሳያስቀሩ” ራሳቸውን ለእርሱ ሙሉ በሙሉ ሰጥተው እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። አክለውም ቅዱስ አውጎስጢኖስ "እግዚአብሔር አዲስ አቅጣጫን፣ አዲስ መንገድን፣ አዲስ ምክንያትን ሰጠው፣ በህይወቱ ብዙ ያተረፈበትን ጸጋ ሰጠው” በእርሱ ውስጥ “እፈልግሃለሁ” የሚለውን የእግዚአብሔር ድምጽ እንደ ሰማ እና በውስጡ ጥልቅ ደስታ እንደተሰማው አክለው አስታውሰዋል።

ፒየር ጆርጎ ፍሬሳቲ፣ የምእመናን መንፈሳዊነት ምልክት

በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይኖር የነበረውን የቅዱስ ፒየር ጆርጂዮ ፍሬሳቲ ወጣት ጣሊያናዊ ሕይወትን፣ በካቶሊክ ማኅበራት ተሳትፎና ድሆችን ማገልገልን ሲገልጹ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት ዛሬም “የፒየር ጆርጆ ሕይወት ለምእመናን መንፈሳዊነት ብርሃን ነው” ሲሉ እምነት የግል ጉዳይ ስላልሆነ በቤተክርስቲያን አባልነት እና ለፖለቲካዊ አገልግሎት ቁርጠኝነት እንደ ነበረው እና ይህም ድሆችን ተጠቃሚ ያደረገ እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።  

ካርሎ አኩቲስ፣ ትሁት የቅድስና ምስክር

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስለ ወጣቱ ጣሊያናዊው ቅዱስ ካርሎ አኩቲስ የዘመናችን ጎረምሳ ምስክርነት ሲናገሩ፣ ጳጳሱ ኢየሱስን በቤተሰቡ ውስጥ እንዴት እንዳጋጠመው ተናግሯል፣ ለወላጆቹ አንድሪያ እና አንቶኒያ ምስጋና ይግባውና ሁለቱ እህቱ ፍራንቼስካ እና ወንድሙ ሚሼል በዚህ በዓል ላይ መገኘታቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስ ካርሎ ደግሞ እምነቱን በትምህርት ቤት አግኝቶ በተግባር ኖረ፣ ነገር ግን በተለይ በቁምስና ማኅበረሰብ ውስጥ የሚከበሩ ሥርዓተ ቅዳሴዎችን በመከታተል ሕይወቱን ለእግዚአብሔር ሰጠ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል “ጸሎትን፣ ስፖርትን፣ ጥናትን እና በጎ አድራጎትን በሕፃንነቱና በወጣትነቱ ጊዜ እንዴት አድርጎ እንዳሳደገው” አስታውሰዋል።

ለእግዚአብሔር እና ለባለእንጀራ ያለንን ፍቅር ማዳበር

ዕለታዊ ቅዳሴ፣ ጸሎት እና በተለይም የቅዱስ ቁርባን ስግደት የቅዱሳን ፒየር ጆርጂዮ እና ካርሎ ለእግዚአብሔር እና ለባለእንጀሮቻቸው ያላቸውን ፍቅር በትህትና የበጎ አድራጎት ተግባራት በማዳበር ሕይወታቸውን ያሳየ ነበር ብለዋል ሊቀ ጳጳሱ። ጳጳሱ አክለው እንደ ገለጹት ከሆነ በሽታ ሁለቱን ሕይወታቸውን በማሳጠር ለተስፋ መመሥከራቸውንና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንዲችሉ አድርጓቸው ነበር ያሉ ሲሆን ወጣቱ ካርሎ “ሰማይ ሁል ጊዜ እየጠበቀን ነው፣ እና ነገን መውደድ ዛሬ ምርጡን ፍሬ መስጠት ነው” ሲል መናገሩን አክለው ገልጸዋል።

የሕይወታችንን “ታላቅ ቅርስ” መሥራት

በማጠቃለያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሁለቱም ቅዱሳን ፒየር ጆርጂዮ ፍሬሳቲ እና ካርሎ አኩቲስ ሁሉንም ሰው “በተለይም ወጣቶች ሕይወታቸውን እንዲያባክኑ ሳይሆን ወደ ላይ ወደ ሰማይ እንዲመሩ እና ድንቅ ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ” እንዴት እንደሚጋብዟቸው አስምረውበታል።

ቅዱስ ካርሎ እንደሚለው “እኔ አይደለሁም እግዚአብሔር  ነው እንጂ” በማለት በቃላቸው ያበረታቱናል። እናም ቅዱስ ፒየር ጆርጂዮ ደግሞ “በሁሉም የተግባሮችህ ማዕከል አምላክ ካለህ መጨረሻ ላይ ትደርሳለህ። ይህ ቀላል ነገር ነው፣ ነገር ግን አሸናፊው የቅድስናቸው ቀመር ነው፣ ሕይወትን በሙላት ለመደሰት እና በሰማያዊው በዓል ጌታን ለማግኘት እንድንከተለው የተጠራንበት ምስክርነት ነው ሲሉ ቅዱስነታቸው ከተናገሩ በኋላ ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 

08 Sep 2025, 14:51