MAP

ር.ሊ.ጳ ሊዮ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ር.ሊ.ጳ ሊዮ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ   (@Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ሊዮ ኢየሱስ ያስተማረን ጩኸት የድካም ሳይሆን የተስፋ ተግባር ነው ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋችን ነው!” በሚለው የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ረቡዕ ጳጉሜ 05/2017 ዓ.ም ያደረጉት የክፍል ስድስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ "ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ" (ማርቆስ 15፡37) በሚለው ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተበትን ሁኔታ በሚገልጸው የምጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው ባደርጉት አስተምህሮ "ኢየሱስ ያስተማረን ጩኸት፣ የድካም ምልክት ሳይሆን የተስፋ ተግባር ነው" ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ

የኢየሱስ መሞት

ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፥ “ኤሎሄ፥ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፥ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፥ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ። ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የሆመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ከዚያም፥ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ። ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፥ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አለ (ማር. 15፡33-39)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

ዛሬ ኢየሱስ በዚህ ዓለም ስለነበረው የሕይወት ፍጻሜ ሁኔታ ላይ እናሰላለን፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞቱን በተመለከተ ማለት ነው። ወንጌላት ስለዚህ ጉዳይ እጅግ ውድ የሆነ ዝርዝር ነገርን ያቀርቡልናል፣ ይመሰክራሉ፣ ይህም በእምነት ብልህነት ሊታሰብበት የሚገባ ነው። በመስቀል ላይ ኢየሱስ ጸጥ ብሎ ብቻ አልሞተም፣  ልክ እንደሚነድ ሻማ ቀስ በቀስ አይጠፋም፣ ይልቁንም በጩኸት ህይወቱን አሳልፎ ሰጠ፥ "ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ" (ማር. 15: 37) ይለናል ቅዱስ ወንጌል። ያ ጩኸት ሁሉንም ነገር ይይዛል፣ ህመም፣ መገለልን ፣ እምነትን እና ራስን አሳልፎ መስጠት ያመልክታል። ይህ አካላዊ የሆነ ድምጽ ብቻ ሳይሆን የመሰጠት የመጨረሻ ምልክት ጭምር ነው።

ከኢየሱስ ጩኸት በፊት “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውከኝ?” ከሚል እጅግ በጣም እጅግ የሚገርም ጥያቄ አንዱ ነው። እሱ የመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 22 የመጀመሪያ ቁጥር ላይ የተጠቀሰ ነው፣ ነገር ግን በኢየሱስ ከንፈሮች ላይ ይህ አባባል ነጠላ ክብደት ይይዛል። ሁልጊዜ ከአብ ጋር በጠበቀ ኅብረት ይኖር የነበረው ወልድ፣ አሁን ዝምታን፣ መተውን፣ የጠለቀ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለ ሆኖ ይሰማዋል። ይህ የእምነት ቀውስ ሳይሆን እስከ መጨረሻው የሚሰጥ የፍቅር የመጨረሻ ደረጃ ነው። የኢየሱስ ጩኸት ተስፋ መቁረጥ አይደለም፣ ነገር ግን ቅንነትን እና እውነትን እስከ ገደቡ ድረስ ተወስዷል፣ ሁሉም ጸጥ ባሉበት ጊዜ እንኳን የሚጸና እምነት ነው።

በዚያን ጊዜ፣ ሰማዩ ጨለመ እና የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ለሁለት ተከፈለ (ማር. 15፡33፣38)። ፍጥረት ራሱ በዚያ ሥቃይ ውስጥ እንደሚሳተፍ እና በተመሳሳይ ጊዜ አዲስ ነገር እንደሚገለጥ ያሳያል። እግዚአብሔር ከአሁን በኋላ ከመጋረጃው ጀርባ አይሆንም - ፊቱ አሁን በተሰቀለው ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይታያል። በዚያ በተሰበረ ሰው ውስጥ ትልቁ ፍቅር እራሱን የሚገልጠው እዚያ ነው። እሩቅ የማይሆነውን፣ ነገር ግን ህመማችንን እስከ መጨረሻው የሚያስታግሰውን አምላክን ማወቅ የምንችለው እዚያ ነው።

አረማዊ የነበረው የመቶ አለቃው ይህንን ተረድቷል። ኢየሱስን “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ” ሲል መናገሩ የሚታወቅ ሲሆን ሲሞት ስላየ እንጂ ንግግሩን ስለሰማ አልነበረም ይህንን የተናገረው (ማር 15:39) ከኢየሱስ ሞት በኋላ የተሰጠ የመጀመሪያው የእምነት መግለጫ ነው። በነፋስ የማይጠፋ፣ ልብን የነካ የልቅሶ ፍሬ ነው። አንዳንዴ በቃላት መናገር የማንችለውን በድምፅ እንገልፃለን። ልብ ሲሞላ ያለቅሳል። እና ይህ ሁልጊዜ የድክመት ምልክት አይደለም፣ የሰው ልጅ ጥልቅ ተግባር ሊሆን ይችላል።

እንደ ሥርዓት አልበኝነትን፣ መጮህን፣ መገፋትን ማሰብ ለምደናል። ወንጌል ለጩኸታችን ትልቅ ዋጋ ሰጥዋል፣  ይህም ጥሪ፣ ተቃውሞ፣ ፍላጎት፣ እጅ መስጠት ሊሆን እንደሚችል ያስታውሰናል። ምንም እንኳን ቃላት በማይኖሩበት ጊዜ ጽንፈኛ የጸሎት ዓይነት ሊሆን ይችላል። በዚያ ጩኸት፣ ኢየሱስ ለተረሱት ሁሉ፣ ፍቅሩን፣ ተስፋውን ሁሉ ሰጠ።

አዎን በመጮኽ ውስጥ ይህ ደግሞ አለ፣ ተስፋ አለመቁረጥ። አንድ ሰው አሁንም መሰማት እንደሚችል ሲያምን ያለቅሳል። ሰው የሚያለቅሰው በተስፋ መቁረጥ ሳይሆን በፍላጎት ነው። ኢየሱስ አባቱን ለመቃረን አልጮኸም፣ ነገር ግን ለእርሱ ነው የጮኸው። በጸጥታ ውስጥ እኳን አባቱ በእዚያ ስፍራ እንዳለ ያውቃል። እናም በዚህ መንገድ፣ ሁሉም ነገር የጠፋ በሚመስልበት ጊዜ እንኳን ተስፋችን ሊጮህ እንደሚችል አሳይቶናል።

ስለዚህ መጮህ መንፈሳዊ ምልክት ይሆናል። ስንወለድ እያለቀስን ወደ አለም የመጣንበት የተወለድንበት ሁኔታ የመጀመሪያ ተግባር ብቻ ሳይሆን፡ በህይወት የመቆየት መንገድም ነው። አንድ ሰው ሲሰቃይ ያለቅሳል፣ ነገር ግን አንድ ሰው ሲወድ የወደደውን ሰው ስም ይጠራል።   መጮህ ማን እንደሆንን መናገር ነው፣ በዝምታ መጥፋት አንፈልግም፣ አሁንም የምናቀርበው ነገር አለን ማለት ነው።

በህይወት ጉዞ ውስጥ አንድን ነገር በውስጣችን ስናቆይ ቀስ በቀስ እኛን ሊበላን የሚችልባቸው ጊዜያት አሉ። ኢየሱስ ቅን፣ ትሁት፣ ለአብ የተላከ እስከሆነ ድረስ መጮህ እንዳንፈራ አስተምሮናል። ለቅሶ ወይም ጩኸት በፍቅር የተወለደ ከሆነ ከንቱ አይደለም። እናም ለእግዚአብሔር የተሰጠ ከሆነ ፈጽሞ ችላ አይባልም። ሌላ ዓለም ይቻላል ብሎ ማመንን ለመቀጠል እምነት የጎደለው እና አሉታዊ አመለካከት ያለመሸነፍ መንገድ ነው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ይህንም ከጌታ ኢየሱስ እንማር፡ የስቃይ ጊዜ ሲመጣ የተስፋ ጩኸት መጮኽህን ከኢየሱስ እንማር። ለመጎዳት ሳይሆን ራሳችን በአደራ ለመስጠት ማለት ነው። በአንድ ሰው ላይ ለመጮህ ሳይሆን ልባችንን ለመክፈት። ጩኸታችን እውነተኛ ከሆነ፣ የአዲስ ብርሃን፣ የአዲስ ልደት መግቢያ ሊሆን ይችላል። ልክ እንደ ኢየሱስ፡ ሁሉም ነገር ያለቀ ሲመስል፣ በእውነቱ መዳን መምጣት ሊጀምር ነው። በእግዚአብሔር ልጆች እምነት እና ነፃነት ከተገለጠ፣ ከክርስቶስ ድምጽ ጋር የተዋሃደው የሰውነታችን የመከራ ድምጽ ለእኛም ሆነ በዙሪያችን ላሉ ሰዎች የተስፋ ምንጭ ይሆናል።

10 Sep 2025, 13:18

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >