MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ "ቤተ ክርስቲያን ዘወትር የትሕትና መማሪያ ሥፍራ ልትሆን ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ጋር ሆነው ያደረሱትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከመምራታቸው አስቀድመው ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ከሉቃስ ወንጌል ምዕ. 14: 1, 7-14 ድረስ በተጻፈው ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ዘወትር የትህትና መማሪያ ቦታ ልትሆን እንደሚገባ በማሳሰብ፥ የሁሉ ሰው ማረፊያ እንድትሆንም ጸልየዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እሁድ ነሐሴ 25/2017 ዓ. ም. እኩለ ቀን ላይ በመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ለተገኙት ምእመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና ጎብኝዎች በዕለቱ የተነበበው የወንጌል ክፍል ስለ ትህትና፣ ስለ ግልጽነት እና ስለ እርስ በርስ ግንኙነት ባህል አስፈላጊነት መናገሩን አስታውሰዋል።

“በዚህ የወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ከዋነኞቹ ፈሪሳውያን መካከል በአንዱ የቀረበለትን ግብዣ መቀበሉ በሁሉም ባሕል ውስጥ በጠረጴዛ ዙሪያ አብሮ መቀመጥ የሰላም፣ የኅብረት፣ የመጋራት እና የመገናኘት ምልክት እንደሆነ የሚያስታውስ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

እውነተኛ የእርስ በርስ ግንኙነት ሁልጊዜ ቀላል እንዳልሆነ የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሃይማኖት መሪውን ቤት የጎበኘው እያስተማራቸው በትህትና፣ በግልጽነት እና በቅንነት መሆኑንም አስታውሰዋል። 

ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለቱ ባቀረበው አስተምህሮው፥ የክብር ቦታን ለመውሰድ ከሚጣደፉ ሰዎች ጋር ተመሳሳይነት ያለውን ምሳሌ የነገራቸው ሲሆን፥ ምናልባትም ተፈላጊነታቸውን ለማሳየት እና ለመታወቅ ይህም በወንድማማችነት፣ በመጋራት እና በትህትና ከመሆን ይልቅ የፉክክር ስሜት የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስን ማዳመጥ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በተመሳሳይ መልኩ ምዕመናን ወደ ቅዱስ ቁርባን ማዕድ ዙሪያ ሲሰበሰቡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረውን ማዳመጥ እንደሚገባ አሳስበው፥ “በተወሰነ መልኩ ኢየሱስ ክርስቶስ እንግዳችን ሆኖ የሚያየን መሆኑን ይነግረናል” ብለዋል። “እራሳችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ዓይን ለማየት መሞከሩ አስፈላጊ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በተደጋጋሚ እርስ በርስ በመፎካከር እውቅናን በማግኘት ወይም ራሳችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ላይ ብቻ ልናተኩር እንደምንችል ተናግረዋል። ልባችንን ለሚፈታትኑ ቃላት ቅድሚያን በመስጠት ማሰላሰልን አቁመን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠንን ነፃነት ማጣጣም ይገባል” ብለዋል።


ትህትና ለእውነተኛ ነፃነት ያዘጋጃል

“ትሕትና እውነተኛ ነፃነትን እንደሚያስገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ይገልጻል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥  “ትሕትና በእውነት ከራሳችን ነፃ መውጣት ነው” ብለው፥ “ከራሳችን አልፈን የሕይወት አድማሳችንን ሰፋ አድርገን ስንመለከተው የእግዚአብሔር መንግሥት እና ጽድቁ በእውነት እንደሚያስፈልገን እናውቃለን” ብለው፥ “ነገር ግን ራሳችንን ከፍ ስናደርግ ወይም በራሳችን ላይ ብቻ ካተኮርን የእግዚአብሔር ውድ ልጆች መሆናችንን እና ከዚህ እውነታ የሚመጣውን የላቀ ክብር እናጣለን” ብለዋል።

“ቀዳሚውን ቦታ ለመያዝ ከመታገል ይልቅ የመጨረሻውን ቦታ መያዝን ከተማርን ያ ክብር እንደሚገለጥ እና ያለ ምንም ጥረት በቀላሉ ወደ ፊት እንመጣለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከመምራታቸው በፊት ባሰሙት የማጠቃለያ ንግግር፥ "ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ሰው የትህትና መማሪያ ቦታ እንድትሆን መጸለይ እንደሚገባ አሳስበው፥ “ቤተ ክርስቲያን ሁሉም ሰው የሚስተናገድባት ቦታ እንደሆነች፣ ፉክክር ተወግዶ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ለእኛ የሚናገርበት እና እርሱ የትህትና እና የነፃነት መንገድ የሚያስተምረን መሆኑን ካስረዱ በኋላ፥ “የዚህ ቤት እናት ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንደ ጸሎታችንን እናቀርባለን” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

01 Sep 2025, 16:49