MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሆነው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሆነው  (@Vatican Media)

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የጥቅምት ወር መርሃ ግብር ይፋ መደረጉ ተገለጸ

በኢዮቤልዩ ዓመት ልዩ ልዩ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የመስከተረም እና የጥቅምት ወር መርሃ ግብር ይፋ ተደርጓል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ የቨነዙዌላው “የድሆች ዶክተር” ብጹዕ ሆሴ ግሪጎሪዮ ሄርናንዴዝ ሲስኔሮስን ጨምሮ የሰባት ብፁዓን ቅድስና የሚታወጅ ሲሆን፥ በወሩ መገባደጃ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚመሩ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመጪዎቹ መስከረም እና ጥቅምት ወራት ውስጥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባዩ በርካታ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች እንደሚፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መስከረም 25/2018 ዓ. ም. ጠዋት የሚስዮናውያን እና የስደተኞች ኢዮቤልዩ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚያሳርጉ ታውቋል። ከአራት ቀናት በኋላ ማለትም ሐሙስ መስከረም 29/2018 ዓ. ም. የገዳማውያን ኢዮቤልዩ በዓል እንደሚከበርም ታውቋል።

እሑድ ጥቅምት 2/2018 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ማኅበራት የተጋጀውን የኢዮቤልዩ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን የሚመሩ ሲሆን፥ ከአንድ ሳምንት በኋላ ማለትም ጥቅምት 9/2018 ዓ. ም. በሚከበረው የተልዕኮ ቀን እሁድ ለሰባት ብፁዓን የቅድስና ማዕረግ እንደሚሰጡ ታውቋል።

ከእነዚህም መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1915 ዓ. ም. በተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል የተገደለው አርሜናዊው የማርዲን ሰማዕት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢግናጤዎስ ቹክራላህ ማሎያን ይገኙበታል። ጃፓኖች በፓፑዋ ኒው ጊኒ ውስጥ የክርስትናን እምነት እንዳይሰብክ ቢከለክሉም የትምህርተ ክርስቶስ መምህርነቱን በመቀጠሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1945 ዓ. ም. በሰማዕትነት ያረፈው የብጹዕ ፒተር ቶ ሮት ቅድስና የሚታወጅ ሲሆን፥ ብፁዕ ፒተር የፓፑዋ ኒው ጊኒ የመጀመሪያው ቅዱስ እንደሚሆን ታውቋል።

እንዲሁም በጣሊያን ቬሮና ከተማ የምሕረት እህቶች ማኅበር መሥራች የሆነች የቪንቼንሳ ማርያ ፖሎኒ ቅድስና የሚታወጅ ሲሆን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች ማኅበር መሥራች ማርያ ዴል ሞንቴ ካርሜሎ ሬንዲልስ ማርቲኔዝ እና የክርስቲያኖች ረዳት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች ማኅበር ገዳማዊ እህት የማርያ ትሮንካቲ ቅድስናም እንደሚታወጅ ታውቋል።

በዚሁ ዕለቱ ሁለት ምእመናን ማለትም ቨነዙዌላዊው ዶክተር፣ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ሦስተኛ ማኅበር አባል እና የተቸገሩትን በማከም አልፎ ተርፎም የሕክምና ወጪዎችን ከኪሱ የሚከፍል በመሆኑ “የድሆች ሐኪም” በመባል የሚጠራው ሆሴ ግሬጎሪዮ ሄርናንዴዝ ሲስኔሮስ እና በጣሊያን ውስጥ እጅግ የተወደደው የፖምፔ ቤተ መቅደስ መሥራች ባርቶሎ ሎንጎ ቅድስና ይፋ እንደሚሆን ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጥቅምት 16/2018 ዓ. ም. በሀገረ ስብከት፣ በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ ለሚያገለግሉ ከሐዋርያዊ ምክር ቤቶች እና ኤኮኖሚ ምክር ቤቶች የተውጣጡ የሲኖዶስ ቡድኖች የሚሳተፉበትን የኢዮቤልዩ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚመሩ ሲሆን፥ በመጨረሻም ሰኞ ጥቅምት 17/2018 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ለትምህርት ዘመን መጀመሪያ የሚቀርብ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ ታውቋል።

 

02 Sep 2025, 17:18