ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ፍጥረታትን መንከባከብ ጥሪያችን ነው” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘውን የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደርን ዓርብ ነሐሴ 30/2017 ዓ. ም. መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ መንደሩ ‘የተስፋ ዘር’ እና ለሥነ-ምህዳር ለውጥ ተጨባጭ ሞዴል ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተወጠነው ይህ ፕሮጀክት መንፈሳዊነትን፣ ትምህርትን፣ ታሪክን፣ ተፈጥሮን፣ ጥበብን እና ቀጣይነት ያለውን የፈጠራ ሥራን አንድ ላይ በማድረግ፥ ቤተ ክርስቲያን ለፍጥረት እና ለጉዳት ለተጋለጡት ለምታደረገው እንክብካቤ ህያው ምስክር እንደ ሆነ ተገልጿል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ወደ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ሲደርሱ ከምዕመናን እና መንደሩን ለመጎብኘት ከመጡት እንግዶች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ግራ እና ቀኙ በዛፍ የተሸፈነውን መንገድ ይዘው ሲራመዱ በቦታው ለነበሩት ቤተሰቦች ሰላምታ የሰጡ ሲሆን፥ በኋላም የመልካም አቀባበል ዋና ጭብጥ ተደርጎ የተገለጸው የፍጥረት እንክብካቤ ከአብሮነት እና ከሰብዓዊ ክብር ጋር አንድነት ያለው መርህ እንደ ሆነ ተገልጿል።
ሁለገብ ሥነ-ምህዳርን ለማሳደግ የቀረበ ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መንደሩን በኤሌትሪክ መኪና በጎበኙበት ወቅት ፕሮጀክቱ ለዘላቂ ዕድገት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል። በዘንድሮው የበጋ ወቅት መጀመሪያ ላይ የፍጥረት ጥበቃን በማስመልከት በአዲሱ የአምልኮ ሥርዓት የመጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን ባቀረቡበት ቦታ የምትገኝ ትንሿን እና ታሪካዊ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልትን ጎብኝተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓሥራ አራተኛ፥ “የተፈጥሮ ካቴድራል” ብለው በጠሩት የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ውስጥ ባደረጉት ንግግር፥ ሰዎች በሙሉ በአኗኗር ዘይቤዎቻቸው ላይ በማሰላልሰል እና የጋራ መኖሪያ ምድርን በመንከባከብ ወደ ሥነ-ምህዳር ለውጥ እንዲመለሱ በድጋሚ በመጋበዝ ሃላፊነትን የበለጠ እንዲወስዱ አሳስበዋል።
ጥንታዊ የሕንጻ ፍርስራሾችን የአትክልት ሥፍራዎችን በጎበኙበት ወቅት በቦታው ከነበሩት ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተው፥ ለመሬቱ እና በመሬቱ ላይ ለበቀሉት ከ3,000 በላይ የእጽዋት ዝርያዎች ለሚያደርጉት እንክብካቤ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ አበቦች በሚገኙበት ኩሬ ውስጥ ያሉ የጃፓን የዓሣ ዝሪያዎች በመመገብ፥ በሥፍራው ውበት ላይም አሰላስለዋል። በወይን የአትክልት ሥፍራ ከሚገኙት የእርሻ ሠራተኞች ጋር ሰላምታ ተለዋውጠው፥ የሚያማምሩ ፈረሶችን ጨምሮ በመስኩ የነበሩትን እንስሳት ባርከዋል።
በ ‘ግሪን ሃውስ’ ውስጥ የተፈጸመ ሥነ-ሥርዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓሥራ አራተኛ በጉብኝታቸው ማጠቃለያ፥ አዲስ የተገነባውን እና ለ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ፕሮጀክት ልብ ሆኖ የሚያገለግለውን የባለ ብዙ ተግባር እና የተጣራ ‘ኢነርጂ ግሪን ሃውስ’ ሕንጻን ጎብኝተዋል። እንዲሁም ለሥነ-ምህዳር ዘላቂነት የሚያግዙ ሁሉ ዓይነት ተነሳሽነቶችን ለማስተናገድ ታቅዶ የተሠራውን የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ዋና መሥሪያ ቤትንም ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው ከቡራኬው ሥነ-ሥርዓት ቀደም ብሎ ከምስጋና ጋር የቀረበውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የመሩ ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እውቁ ጣሊያናዊ የዜማ ደራሲ አንድሬያ ቦቼሊ ከልጁ ማቴዎ ጋር ዜማን አሰምቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ በተጻፈው ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “የሰማይ ወፎችን እና የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ” ሲል ያቀረበውን ግብዣ በማስታወስ፥ እያንዳንዱ ፍጡር በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ ጠቃሚ እና የተለየ ሚና ያለው በመሆኑ መልካም ነው” ብለዋል።
“ፍጥረትን መንከባከብ በእርግጥም የእያንዳንዱ ሰው ጥሪ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “እኛ በፍጡራን መካከል ፍጥረትን እንድንከባከብ ከፈጣሪው ኃላፊነት የተጣለብን ፍጥረታት ነን” ብለው፥ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር እምነትን እና ቀጣይነትን ታሳቢ እንዲያደርግ ታቅዶ የተዘጋጀ ሥፍራ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ዛሬ የምናየው ይህ ሥፍራ መንፈሳዊነት፣ የዕለት ተዕለት ኑሮ እና ቴክኖሎጂ ተስማምተው የሚኖሩበት ልዩ ውበት ያለበት ነው” ብለው፥ የፍትህ እና የሰላም ፍሬን ማፍራት የሚችል የእርስ በርስ መቀራረብ መሳሌ መሆኑንም ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።
ስለፍጥረት የቀረበ ጸሎት
የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር የምረቃ ሥነ-ሥርዓት፥ እግዚአብሔርን ለፍጥረታቱ በማመስገን፣ መሪዎችን የጋራ ጥቅምን እንዲያስተዋውቁ እና እንዲሁም የሰው ልጅ ሕይወትን ለመጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማጠናከር፥ “የፍትሕ፣ የሰላም፣ የፍቅር እና የውበት መንግሥት እንዲመሠርቱ በማሳሰብ ተጠናቅቋል።