MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ድሆችን ከሚረዳ የቅዱስ ፍራንችስኮስ የበጎ ተግባር ማኅበር አባላት ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ድሆችን ከሚረዳ የቅዱስ ፍራንችስኮስ የበጎ ተግባር ማኅበር አባላት ጋር  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የበጎ አድራጎት ሥራ ሕይወትን እንደሚለውጥ እና ኅብረትን እንደሚገነባ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ድሆችን ከሚረዳ የቅዱስ ፍራንችስኮስ የበጎ ተግባር ማዕከል አባላት ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ የበጎ አድራጎት ሥራቸውን ዕርዳታን በማድረግ፣ የተቸገሩትን በመቀበል፣ ሰብዓዊ ክብርን በማስተዋወቅ እና የእግዚአብሔርን ፍቅር በኅብረተሰብ ዘንድ በተጨባጭ እንዲመሰክሩ አሳስበዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቅዱስ ፍራንችስኮስ የበጎ ተግባር ማዕከል አባላትን ሰኞ ነሐሴ 26/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ለሰው ልጅ ክብርን የመስጠት፣ የመልካም አቀባበል እና የእንክብካቤ ተልእኳቸውን በታማኝነት እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።

ቅዱስነታቸው በሰሜን ጣሊያን ሚላን ከተማ ውስጥ ከሚገኝ ተቋም ለመጡት ልዑካን ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ ማዕከሉ ለሰባት አስርት ዓመታት በሚጠጋ ጊዜ ከ30,000 ለሚበልጡ ሰዎች የምግብ፣ የአልባሳት እና የሕክምና አገልግሎት እና ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱ ታውቋል።

“የቅዱስ ፍራንችስኮስ የበጎ ተግባር ማኅበር አባላትን በደስታ ተቀብያቸዋለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ማዕከሉ ለተቸገሩት ሰዎች የሚያደርገውን ዕርዳታ እና መስተንግዶ በማረጋገጥ፥ ከክርስቲያናዊ ዓርዓያነት በተጨማሪ በፍራንችስካዊ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የሰውን ልጅ ሙሉ ሰብዓዊ ዕድገት ለማጎልበት ወደ ሰባ ለሚጠጉ ዓመታት ሠርቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

የካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር አባል በሆኑት በወንድም ቼቺሊዮ ማርያ ኮርቲኖቪስ ልብ ውስጥ ያለውን ተነሳሽነት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “እናንተ ዛሬ በተግባር የምትመሰክሩት እና ዋና ተዋናይ የሆናችሁበት ተግባር ከእምነት እና ከለጋስነት የመነጨ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የበጎ አድራጎት ሥራ ሦስት ገጽታዎች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በንግግራቸው፥ የቅዱስ ፍራንችስኮስ የበጎ ተግባር ማኅበር   ሥራ ሦስት ገጽታዎችን ሲገልጹ፥ “የተቸገረን መርዳት፣ በእንግድነት መቀበል እና ማስተዋወቅ መሆኑን አስምረውበታል። 

“የተቸገረን መርዳት ማለት የሌሎችን ፍላጎቶች ማሟላት ማለት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በዓመታት ውስጥ ወደ ማዕከላቸው የሚመጡትን ለመርዳት መቻላቸውን ማየት እጅግ አስደናቂ እንደሆነ ተናግረው፥ ይህ ማዕከል በየዓመቱ ከሰላሳ ሺህ በላይ ሰዎችን በተለያዩ መንገዶች የሚደግፍ መሆኑን አስታውሰዋል።

ማዕከሉ ዕርዳታን ከመስጠት ጎን ለጎን የተቸገሩትን በእንግድነት እንደሚቀብል ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “በልብ ውስጥ ለሌላ ሰው ሕይወት ቦታን ማዘጋጀት፣ ጊዜ መስጠት፣ ማዳመጥ፣ መደገፍ እና መጸለይ፥ እነዚህ በሙሉ ለነፍስሔር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድሆችን በዓይን የመመልከት፣ የመጨባበጥ እና የመቅረብ ተግባራት ናቸው” ሲሉ አስታውሰዋል።

በመጨረሻም፥ “ድሆችን ማስተወቅ ማለት በነጻነት እና በክብር እንዲያድጉ መርዳት ማለት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በዚህ ስጦታ ውስጥ ለሰው ልጅ የሚሰጥ ክብር ወደ ተግባር እንደሚለወጥ አስረድተው፥ በመሆኑም አንድ ሰው ለሚገኟቸው ሰዎች የሚጨነቀው በምላሹ ጥቅማ ጥቅሞችን ለማግኘት ሳይሆን ሁኔታዎች እንደሚያስገድዱት አስረድተዋል። እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ላይ እንደሚያደርገው ሁሉ  የሚያስፈልገንን ዕርዳታ ሁሉ በመስጠት መጓዝ ያለብንን መንገድ እንደሚያመለክተን አስረድተዋል።   

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቃላትን በማስታወስ እንደተናገሩት፥  “የእያንዳንዱን ሰው ክብር እና የፈጠራ ችሎታ በብቃት የማሳደግ፣ ለሥራቸው ጥሪ ምላሽ የመስጠት ችሎታው እና በውስጡ የያዘውን የእግዚአብሔር ጥሪን መቀበል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ለቤተ ክርስቲያን እና ለኅብረተሰብ የተሰጠ ተልዕኮ

“ውድ ወዳጆቼ ይህ በምታስተዳድሩት ማዕከል ዙሪያ ለሚሰበሰቡ ሰዎች እና ጠቅላላ ኅብረተሰብን እንዲጠቅም ቤተ ክርስቲያን በአደራ የሰጠቻችሁ ተግባር ነው” ሲሉ አረጋግጠው፥ በማጠቃለያቸው አባላቱን ለሥራቸው እና አብረው በመጓዝ ለሚሰጡት ምሥክርነት በማመስገን ሐዋርያዊ ቡራኬውን በመስጠት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

01 Sep 2025, 17:04