ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የመሣሪያ ድምጽ ጠፍቶ የወንድማማችነት እና የፍትህ ድምጽ እንዲሰፍን ተማጸኑ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሩሲያ በዩክሬን በሚገኙ ከተሞች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት እያጠናከረች በሄደችበት ወቅት በአፋጣኝ ተኩስ ቆሞ ከፍተኛ የውይይት ጥረት እንዲደረግ ጥሪያቸውን ደግመው አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እሁድ ነሐሴ 25/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት የሰላም ጥሪያቸው የጦር መሣሪያዎች ድምጽ ጠፍቶ የወንድማማችነት እና የፍትህ ድምጽ እንዲሰማ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ ነሐሴ 25/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ጋር ሆነው ካደረሱት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አስቀድመው ባደረጉት ንግግር፥ በዩክሬን ያለው ጦርነት በሚያስከትላቸው ተከታታይ ውድመቶች እና የሰው ሕይወት መጥፋት የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ ከዩክሬን ሕዝብ ጋር ያላቸውን መቀራረብ አድሰዋል።
ሁሉም ሰው ከግዴለሽነት በመራቅ ይልቁንም በጸሎት እና በተጨባጭ የበጎ አድራጎት ተግባራት እንዲቀራረብ በማሳሰብ የተኩስ አቁም ጥሪያቸውን በድጋሚ አቅርበው፥ “በስልጣን ላይ የሚገኙት ሰዎች በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድጋፍ ከጦርነት ይልቅ ወደ ድርድር ገበታ ተመልሰው በሰላም መንገድ ላይ የሚጓዙበት ጊዜ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በሚኒያፖሊስ ትምህርት ቤት የተገደሉትን በጸሎቶች አስታውሰዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ ተመልሰው ባሰሙት ንግግር፥ በዩናይትድ ስቴትስ ሚኒሶታ ከተማ በሚገኝ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ በጥይት የተገደሉትን በጸሎት በማስታወስ፥ “በዓለም ዙሪያ በየቀኑ የሚገደሉትን እና የሚጎዱትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕጻናትን በጸሎታችን እናስታውስ” ብለው፥ “ዓለማችንን የሚያጠቃ የቀላል ሆነ የከባድ የጦር መሣሪያ ወረርሽኝ እንዲያቆም እግዚአብሔርን እንለምነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ የነብዩ ኢሳይያስ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ የሰው ልጆች ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፣ ጦራቸውንም ወደ ማጭድ እንዲለውጡ የሰላም ንግሥት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳቸው ጸሎት አቅርበዋል።
ቅዱስነታቸው በሞሪታኒያ የባሕር ዳርቻ የሞቱትን ስደተኞች አስታወሱ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሞሪታንያ የባሕር ዳርቻ ስደተኞችን አሳፍራ የነበረች መርከብ ስትገለበጥ የሞቱ ቢያንስ 69 ሰዎችን እና ወደ 100 የሚጠጉት የጠፉትን በጸሎታቸው አታውሰዋል።
በዚህ አደጋ እስካሁን 17 ሰዎች ሕይወት መትረፋቸው ሲነገር፥ ጀልባዋ ማክሰኞ ነሐሴ 20/2017 ዓ. ም. ከመስጠሟ ከ6 ቀናት በፊት ከጋምቢያ መነሳቷን በሕይወት የተረፉት ሰዎች ተናግረዋል።
“ይህ አደጋ በዓለም ዙሪያ በየቀኑ ይከሰታል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ፥ “እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በተግባር እንድናውለው እንደ ግለሰብ እና እንደ ማኅበረሰብ እግዚአብሔር እኛን እንዲያስተምረን እንጸልይ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው ማጠቃለያ በአደጋው የሞቱትን ሰዎች በሙሉ በጸሎታቸው በማስታወስ፥ “በየቦታው የተጎዱትን፣ የጠፉትን እና የሞቱትን በሙሉ ወደ አዳኛችን አፍቃሪ እቅፍ እናቀርባለን” ብለዋል።