ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ገዳማውያን በዓለም ዙሪያ አንድነትን እንዲያበረታቱ ጠየቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅዱስ አጎስጢኖስ ዓለም አቀፍ ገዳማውያን ማኅበር አባል የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የማኅበራቸው ጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤ መክፈቻን በማስመልከት ሰኞ ነሐሴ 26/2017 ዓ. ም. በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ቃለ-ምዕዳን አሰምተዋል። በቃለ-ምዕዳናቸው የማኅበሩ ገዳማውያን እና ገዳማውያት ለአገልግሎታቸው ፍሬያማነት የመንፈስ ቅዱስን እገዛ እንዲለምኑ አሳስበዋል።
“መንፈስ ቅዱስ ዛሬም እንደ ትናንቱ ይናገራል” በማለት በአጽንኦት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤ ድባብ ለዘመናት ከዘለቀው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ጋር በመስማማት እግዚአብሔርን እና ሌሎችን የማዳመጥ ድባብ ሊኖረ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በጉባኤው ላይ ለሚሳተፉት በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “እነዚህን የሚቀጥሉ ቀናት በሚገባ ተጠቅመው ለመግባባት እና ለመረዳት ልባዊ ጥረት በማድረግ የሰማዩ አባት ለጋራ ጥቅም ሲል ወደዚህ ሥፍራ ጠርቷቸው ለሚሰጣቸው የብርሃን እና የጸጋ ስጦታ ለጋስ ምላሽ እንዲሰጡ አደራ ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ንግግራቸውን በመቀጠልም፥ የትኅትናን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ የሰማውን የማኅበሩን መሥራች ቅዱስ አጎስጢኖስን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “በእግዚአብሔር አስደናቂ እና ነፃ ድርጊት ፊት ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ ግብዣ ቀርቦልናል” ብለዋል።
“ለጥያቄዎች መልሶች አሉን” ብሎ ከመገመት ይልቅ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣውን ሃሳብ በእምነት በመቀበል፥ የኢየሱስ ክርስቶስን ቃላት ለመማር እና ለማስታወስ ራስን መፍቀድ ይገባል ብለዋል።
አንድነትን ማሳደግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ በቀረበው የአንድነት እሴት ላይ በማትኮር እንደተናገሩት፥ በመጀመሪያው ንባብ በቀረበው የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት መሠረት የጉባኤው ተሳታፊዎች ለሁሉም በጋራ የሚጠቅም የመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ስጦታን እንዲቀበሉ አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው የመልዕክታቸው ገጽታን ከማብራራታቸው አስቀድመው ከልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች ለመጡት የማኅበሩ አባላት በእንግሊዝኛ እና በጣልያንኛ ቋንቋዎች ተናግረው፥ ገዳማውያኑ ገዳማውያቱ በሙሉ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን እንዲለምኑ አደራ ብለዋል።
“በእርግጥ ሁሉንም ቋንቋዎች የመረዳት ወይም የመናገር ስጦታ ባይኖራችሁም የማዳመጥ፣ ትሁት የመሆን እና በማኅበሩ፣ በመላዋ ቤተ ክርስትያን እና በዓለም ውስጥ አንድነትን የማበረታታት ስጦታ ተሰጥቷችኋል” ሲሉ ተናግረዋል።
“አንድነት የጥረታችሁ ሁሉ ወሳኝ ግብ ይሁን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመቀጠልም፥ “ይህ ብቻ ሳይሆን አንድነታችሁ ተግባራችሁን ለመገምገም እና አብሮ ለመሥራት መመዘኛ ሊሆን ይችላል” ብለው፥ ከእርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣ ሁሉ አንድ የሚያደርግ እንጂ የሚከፋፍል ሊሆን አይችልም” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ስብከታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “በመስዋዕተ ቅዳሴው መጀመሪያ ላይ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ያቀረቡትን ጸሎት በማደስ በጉባኤው መካከል መደማመጥ፣ ትሕትና እና አንድነት እንዲኖር የሚጋብዝ መሆኑን ገልጸው፥ “አባት ሆይ! ካንተ ዘንድ የሚወጣው መንፈስ ቅዱስ አእምሮአችንን በማብራት እንደ ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ወደ እውነት ሁሉ ይምራን” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።