ር.ሊ.ጳ ሊዮ በጦርነት በተጎዱ የዓለም አካባቢዎች በቅድስት ሀገርና ዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን ተማጽነዋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የፒየር ጆርጂዮ ፍሬሳቲ እና የካርሎ አኩቲስ ማዕረገ ቅድስናን ምክንያት በማድረግ የተካሄደውን መስዋዕተ ቅዳሴ ተከትሎ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱሳን እና የድንግል ማርያም አማላጅነት ሁላችንም "እግዚአብሔር ጦርነትን አይፈልግም፣ እግዚአብሔር ሰላም ይፈልጋል!" የሚለውን እድናስተጋባ ይርዳን ማለታቸው ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ሰው ለቅድስት ሀገር፣ ዩክሬን ሕዝቦች እና በጦርነት ለተሰቃዩ የአለም ክፍሎች ጸሎታቸውን ማድረግ እንዲቀጥሉ ምዕመናን አበረታተዋል። ለዓለም መሪዎች “በጦር መሣሪያ፣ ሞትንና ጥፋትን በመዝራት የተገኙ ግልጽ ድሎች በእርግጥ ሽንፈቶች ናቸው እንጂ ሰላምና ደኅንነት አያመጡም” በማለት የኅሊናቸውን ድምፅ እንዲሰሙ ጥሪያቸውን ደጋግሞ አቅርበዋል።
"እግዚአብሔር ጦርነትን አይፈልግም። እግዚአብሔር ሰላም ይፈልጋል! የጥላቻን አዙሪት ለማፍረስ እና በውይይት ጎዳና የሚሄዱትን እግዚአብሔር ይደግፋል" ሲሉ ቅዱስነታቸው ሰላም በአለም ዙሪያ ይሰፍን ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
በሃንጋሪ እና ኢስቶኒያ ውስጥ ሁለት አዳዲስ ብጹዕን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በኢስቶኒያ እና በሃንጋሪ ሀገራት ቤተክርስቲያን ሁለት አዳዲስ ሲመተ ብፅዕናን እያከበረች መሆኑን አስታውሰዋል።
በኢስቶኒያ ዋና ከተማ በሆነችው በታሊን፣ የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል የነበሩ ሊቀ ጳጳስ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች ቅዳሜ ጳጉሜ 01/2017 ዓ.ም ሲመተ ብፅዕና እንደ ተሰጣቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው እ.አ.አ በ 1942 የሶቪየት አገዛዝ በወቅቱ በቤተክርስቲያኗ ላይ ባደረሰው ስደት መገደላቸውን አስታውሰዋል።
እንዲሁም ቅዳሜ እለት፣ በሃንጋሪ ቬዝፕሬም ማሪያ ማግዶልና ቦዲ ሲመተ ብፅዕና እንደ ተሰጣቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው እ.አ.አ በ1945 ዓ.ም አንዲት ወጣት ምእመን ሊያጠቁዋት የሞከሩትን ወታደሮች በመቃወሟ የተነሳ መገደሏን ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቤተክርስቲያን የበለጸገችው በእነዚህ ሁለት አዳዲስ ብፅዕን ደም ምስክርነት ነው ያሉት ሲሆን በተጨማሪም እሁድ ጳጉሜ 02/2017 ዓ.ም በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የቅድስና ማዕረግ አሰጣጥ ክብረ በዓል ላይ ለተሳተፉት፣ ለመላው ጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለኦፊሴላዊ ልዑካን እና ለተከበሩ ባለ ሥልጣናት እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ምእመናን ከሰማንያ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ስላደረጉት ነገር ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።