MAP

በሱዳን የምታየው ሰብዓዊ ቀውስ በሱዳን የምታየው ሰብዓዊ ቀውስ  

ር.ሊ.ጳ ሊዮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሱዳን ለተፈጠረው ቀውስ ምላሽ እንዲሰጥ ተማጸኑ!

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ አስቀቃቂ የሆነ ጦርነት እየተካሄደባት በሚገኘው ሱዳን ለሚሰቃዩት ወገኖች ሰብዓዊ ርዳታ እንዲደረግ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ተማጽነዋል፣ እናም በሀገሪቱ ዳርፉር ግዛት በተከሰተው አውዳሚ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“አሰቃቂ ዜና ከሱዳን እየወጣ ነው፣ በተለይም ዳርፉር በኤል ፋሸር፣ በከተማዋ በርካታ ንፁሀን ዜጎች በታሰሩበት፣ የረሃብ እና የአመጽ ሰለባ በሆኑበት ግዛት የደረሰው አሰቃቂ የመሬት መንሸራተት አደጋ የብዙ ሰዎችን ውድ ሕይወት ቀጥፏል” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ረቡዕ እለት ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም ባደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማብቂያ ተናግረዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩት በዚያ ለሚሰቃዩ ሰዎች ሰብዓዊ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባቀረቡት የተማጽኖ ጥሪ በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ጸሎት ያደረጉ ሲሆን በዚህ ሳምንት በጎርፍ ምክንያት በተከሰተ ከባድ የመሬት ናዳ የተነሳ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በሀገሪቱ ምስራቃዊ የሱዳን ማርራ ተራሮች አከባቢ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተገልጿል።  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሱዳን ለ29 ወራት በዘለቀው ጦርነት የተነሳ ብዙ ሰዎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት የደረሰውን ሞት እና መጠነ ሰፊ መፈናቀል በመጥቀስ፣ “ይህንን ሰብአዊ ቀውስ ለማስቆም የተቀናጀ ምላሽ እንዲሰጥ ለባለድርሻ አካላት እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ልባዊ ጥሪ አቀርባለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ግጭቱን ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲደረግ ጠይቋል፣ “ግጭቱን ለማስቆም እና የሱዳንን ህዝቦች ተስፋ፣ ክብር እና ሰላም ለመመለስ በፓርቲዎች መካከል ከባድ፣ ቅን እና ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት ለመጀመር ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።

በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱት ሰዎች ጸሎት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፡- “ታራሲን በመባል በሚታወቀው ሥፍራ ውስጥ ከባድ የመሬት መንሸራተት ናዳ ለብዙዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፣ ይህም ህመም እና ተስፋ መቁረጥን አስከትሏል። እናም ይህ በቂ ስላልሆነ የኮሌራ መስፋፋት ቀድሞውኑ የተዳከሙትን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል" በማለት በቀጠናው ሰላም ይሰፍን ዘንድ ቅዱስነታቸው ተማጽነዋል።

"እኔ ከምንጊዜውም በላይ ለሱዳናውያን በተለይም ለቤተሰቦች፣ ህጻናት እና ተፈናቃዮች ቅርብ ነኝ። ለተጎጂዎች ሁሉ እጸልያለሁ። በሱዳን ማራ ተራሮች ላይ በተከሰተው የመሬት መሸራተት እና መደርመስ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ሁላችሁም ጸሎት በማድረግ እንድትተባበሩኝ እጠይቃለሁ" ማለታቸው ተገልጿል።

እንዲሁም ለሞቱት የጌታን ዘላለማዊ ሰላም፣ እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እና ብርታትን በመለመን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የተማጽኖ ጥሪያቸውን ደምድመዋል።

03 Sep 2025, 15:39