MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመሩበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመሩበት ወቅት   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ “እስራኤል ኳታር ውስጥ በሃማስ ላይ የፈጸመችው ጥቃት አሳሳቢ ነው” ሲሉ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ከሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ወደ ቫቲካን ሲመለሱ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። እስራኤል በኳታር መዲና ዶሃ ውስጥ በሃማስ ተወካዮች ላይ የፈጸመችውን የቦምብ ጥቃት በማስመልከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ “ነገሮች ወዴት እያመሩ እንደሆነ ስለማናውቅ ለሰላም ብዙ መጸለይ እና መሥራት አለብን” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የጋዛ ነዋሪዎች ከተማውን ለቀው እንዲወጡ ከእስራኤል በኩል ስለ ቀረበው ትእዛዝ እና በጋዛ የሚገኙ የቁምስና ካኅን ለማግኘት ያደረጉትን ጥረት በተመለከተ፥ “ምንም ዜና የለኝም” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እስራኤል በኳታር መዲና ዶሃ ውስጥ የፈጸመችውን የቦምብ ጥቃት ተከትሎ ምላሽ እንዲሰጡ በተጠየቁ ጊዜ፥ በክስተቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ስጋት ገልጸው፥ ጉዳዩን “እጅግ አሳሳቢ” ሲሉ ተናግረዋል። “ጥቃቱ በአንዳንድ የሃማስ መሪዎች ላይ ያነጣጠረ ነው” የተባለ ሲሆን፥ በዋና ከተማዋ ዶሃ ውስጥ በሚገኙ በርካታ የመኖሪያ ሕንፃዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተመልክቷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሰኞ ከሰዓት በኋላ እና ማክሰኞ በከፊል በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ለማሳለፍ ከመረጡበት ወደ ቫቲካን ከመመለሳቸው በፊት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ለሰላም ብዙ መጸለይ እና መሥራት ይገባል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለው ሁኔታ ያላቸውን ስጋት ገልጸው፥ “ሁኔታው በእውነት ከባድ ነው” ብለዋል። “ነገሮች ወዴት እያመሩ እንደሆነ ስለማናውቅ ለሰላም ብዙ መጸለይ፣ መሥራት እና ጥረታችንን አጥብቀን መቀጠል አለብን” ብለዋል።

ነዋሪዎች ጋዛን እንዲለቁ የተሰጠ ትእዛዝ

ጋዛ ውስጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሊባባስ ይችላል ተብሎ በሚታሰብበት በዚህ ወቅት፥ የጋዛ ነዋሪዎች አካባቢውን በአስቸኳይ እንዲለቁ እስራኤል የሰጠችውን ትእዛዝ በማስመልከት ሲናገሩ፥

ጋዛ ውስጥ የሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን መሪ ካኅን አባ ገብርኤል ሮማኔሊን በስልክ ለማነጋገር ሞክረው እንደ ነበር አስረድተው፥ ከዚህ በፊት የነበሩ ሁኔታዎች መልካም እንደ ነበሩ እና  ከአዲሱ የእስራኤል ትዕዛዝ በኋላ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ አይደለሁም” ብለዋል።

የቅዱስነታቸው ወደ ቫቲካን መመለስ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ወደ ቫቲካን ከመመለሳቸው በፊት በሥፍራው ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ የሰጡ ሲሆን፥ በካስቴል ጋንዶልፎ ባሳለፏቸው ጥቂት ቀናት ቀጠሮ የተያዘለት ልዩ ሥነ-ሥርዓት ባይኖራቸውን ዕለታዊ ተግባሮቻቸውን ሲያከናወኑ ቆይተዋል።

 

 

10 Sep 2025, 15:56