ር. ሊ. ጳ. ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ አዲስ ሥነ-ምህዳራዊ እና መንፈሳዊ ምዕራፍ እንደሚያስጀምሩ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከሮም በስተደቡብ ምሥራቅ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የከበረ ማረፊያ እና ለም ሥፍራ ወደ አልባኖ ሐይቅ የሚመለከቱ ሰፋፊ ሕንፃዎች እና የአትክልት ሥፍራዎች ያሉት እንደሆነ ታውቋል። በመጀመሪያ ቦታው የንጉሥ ዶሚቲያን መኖሪያ የሚገኝበት የነበረ ሲሆን፥ በኋላ ላይ ቅድስት መንበር ተቀብላው በታሪክ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጋ ጊዜ ማረፊያ አድርጋው መገልገሏ ይታወሳል።
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ አሥራ አራተኛ እና የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ፕሮጀክት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በያዝነው ሳምንት ውስጥ በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኙትን አብዛኛው ንብረቶችን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሥነ-ምህዳር መንደር ፕሮጄክት ክፍል በማድረግ በይፋ እንደሚከፍቱት ታውቋል። 135 ሄክታር ስፋት ያለው የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የአትክልት፣ የእርሻዎች፣ የሬስቶራንት እና የገበያ ማዕከል ልማት ተነሳሽነት አገልግሎቱን በተለያዩ ቋንቋዎች እንደሚያቀርብ ታውቋል።
የትምህርት ማዕከሉ በአንድ በኩል ለአንድ ቀን ወይም ረዘም ላለ ጊዜ ለሚቆዩ ጎብኝዎች፣ የሀገረ ስብከት እና የቁምስና ቡድኖች፣ ገዳማውያት እና ገዳማውያት፣ ካህናት፣ ጳጳሳት፣ ተማሪ ልጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አቅመ ደካማ ማኅበረሰቦች እና የጳጳሳት ጉባኤዎች ልኡካን ክፍት እንደሚሆን ታውቋል። ማዕከሉ በተለይ ለዋና የሥራ አስፈፃሚዎች፣ ለኢንዱስትሪ መሪዎች እና ለንግዱ ዓለም የተነደፉ ኮርሶችን የሚሰጥ ቢሆንም ወደ ማዕከሉ የሚመጡትን በሙሉ በክብር የሚቀበል መሆኑን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር አስተዳደር ዳይሬክተር አባ ማኑዌል ዶራንቴስ አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስን ራዕይ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፥ ይህን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጋ ጊዜ ማረፊያ ቦታን አስቀድሞ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 ዓ. ም. ለጎብኚዎች ክፍት ያደረጉት እና ተነሳሽነቱን የወሰዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዋና ዓላማቸው ለሥልጠና እና ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ግንዛቤን ለማሳደግ እና ሥነ-ምህዳራዊ ትምህርትን ለማስተዋወቅ መሆኑ ይታወሳል።
በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጋ ጊዜ ማረፊያ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚሰጠው አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ በዘንድሮው የበጋ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የአትክልት ሥፍራዎችን ከጎብኝዎች ጋር ለመጋራት ደስተኛ መሆናቸውን እና ጎብኚዎች ከሄዱ በኋላም ከሰዓት በኋላ በአትክልት ሥፍራው በየዕለቱ የእግር ጉዞን ለማድረግ እና ለመጸለይ መመኘታቸውን አባ ማኑዌል ዶራንቴስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት አስረድተዋል።
በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተሰየመ የወይን ሥፍራ
በብዙ መልኩ በሁለቱም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የታየው በጎነት፥ ሁለቱም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘውን ያማረ አረንጓዴ መንደርን ከመላው ሕዝቡ ጋር ለመጋራት ፈቃደኛ መሆናቸውን የሚያሳይ አስደናቂ ማረጋገጫ መሆኑ ተነግሯል።
በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘውን የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር የሚጎበኙት በሙሉ በቦታው በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት ፊት ቀርበው ጸሎት ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን፥ ከዚህ በፊት የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም የቤተ ክርስቲያንን ሸክም በቤተ ክርስቲያን እናት በቅድስት ድንግል ማርያም ፊት የሚያቀርቡበት ቦታ እንደ ነበር ተገልጿል። ጎብኝዎቹ ጥንታዊውን የሮማውያን ፍርስራሽ፣ የቫቲካን የጠፈር ምርምርን፣ የእርሻ ሥፍራን፣ ታሪካዊ ሐውልቶችን፣ ብርቅዬ የጥበብ ሥራዎችን እና ንብረቶችን መጎብኘት እንደሚችሉ ታውቋል።
ትንሽ የነበረውን የወይን እርሻን በመተካት የተዘጋጀው አዲስ እና ሰፊ የወይን ተክል እርሻ ከጣሊያን ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስም መዘጋጀቱን አባ ማኑኤል ዶራንቴስ ገልጸው፥ እንደ ጎርጎርሳውያኑ በ2029 ዓ. ም. ከእርሻው ወይን መጭመቅ እንደሚቻል ገምተዋል።
በ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር አዲስ የተገነባው ሬስቶራንት ከእርሻው በሚገኙ ምርቶች የተዘጋጁ ምግቦችን የሚያቀርብ ሲሆን፥ ገበያ ማዕከሉ እንደ የወይራ ዘይት፣ ማር፣ ወተት እና ሌሎች ምርቶችን እንደሚያቀር ተነግሯል። ጎብኚዎች እንደ አይብ ማምረት ባሉ ተግባራት ላይ የመሳተፍ ዕድልም እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር መንፈሳዊነት
የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ፕሮጄክት “ወዳሴ ላንተ ይሁን” በተሰኘው የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳት ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳን እንደተገለጸው ሁሉ፥ የቤተ ክርስቲያንን ሁለገብ የሥነ-ምህዳር ራዕይን የያዘ እንደሆነ እና እምነትን ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እና ለሕዝቦቿ ጥቅም ከሚሰጥ ተጨባጭ እንክብካቤ ጋር የሚያገናኝ አካሄድ እንደሆነ ታውቋል። እንደዚሁም የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ፕሮጄክቶች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ በቅለው እንደሚያብቡ ቤተ ክርስቲያን ተስፋ እንደምታደርግ ተነግሯል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅርቡ በንብረትነት የተገነባውን አዲሱን የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል ዓርብ ነሐሴ 30/2017 ዓ. ም. በይፋ መርቀው እንደሚከፍቱት ሲጠበቅ፥ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ሲውል በ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” ቃለ-ምዕዳን፣ በ ‘ኦርጋኒክ’ እርሻ፣ ዘላቂነት ባላቸው ልማዶች እና በሥነ-ምህዳር አመራር ላይ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ታውቋል። የማዕከሉ መንፈሳዊነት የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ለመንከባከብ ላለው አስቸኳይ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በተዘጋጁ ስልጠናዎች እንደሚታገዝ ተገልጿል።
ሜክሲኳዊው የ “ወዳሴ ላንተ ይሁን” የሥነ-ምህዳር ፕሮጀክት አስተዳደር ዳይሬክተር አባ ማኑኤል ዶራንተስ በአሜሪካ የቺካጎ ሀገረ ስብከት ካኅን እንደሆኑ ታውቋል።