የጳጳሳት ድምጽ ለሰላም
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
"በቅድስት ሀገር፣ በዩክሬን እና በተለያዩ የአለም ክልሎች በተደረጉ ጦርነቶች መቆሰላችን እየቀጠለ ባለበት ወቅት ምእመናን በሙሉ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም በጾም እና በጸሎት እንዲያሳልፉ እጋብዛለሁ፣ ጌታ ሰላምና ፍትህን እንዲሰጠን እና እየተካሄዱ ባሉ የትጥቅ ግጭቶች ምክንያት የሚሰቃዩትን ሰዎች እንባ እንዲያብስላቸው እምጸናለሁ" ያሉት ሊዮ አሥራ አራተኛ ምእመናን ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓመፅ በተበጣጠሰው ዓለም ውስጥ የማስታረቅን ስጦታ እንዲጎናጸፉ አሳስበዋል። ቤተ ክርስቲያን የሰማይ ንግሥት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን መታሰቢያ ባከበረችበት ዕለት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማርያም በአማላጅነቷ ሰዎች የእርቅን መንገድ ያገኙ ዘንድ፣ “እንዲሁም የሰላም ንግሥት ተብላ ወደ ተጠራች” ወደ እርሷ እንዲመለሱ ጳጳሱ አሳስበዋል።
በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካደረጉ በኋላ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አርብ እለት ሁሉም ሰው ወደ ድንግል ማርያም "ንግሥት" ተብላ በምትታሰብበት እለት እንዲጸልዩ ጋብዘዋል።
ሁላችንም እርቅ ፈጣሪ ሰዎች እንሁን!
በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቀጠለው ተነሳሽነት የቀደሙት የንፍስኄር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ፈለግ ተከትሎ ነው፣ በጵጵስና ዘመናቸው በነበሩት አሥራ ሁለት ዓመታት፣ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ እና “በስቃይ ላይ በምትገኘው ዩክሬን” ውስጥ የሰላም ጥሪዎችን በተደጋጋሚ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ቀድሞውኑ እ.አ.አ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም ለጵጵስና ከተመረጡ ከስድስት ወራት በኋላ፣ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሶሪያ፣ ለመካከለኛው ምስራቅ እና ለመላው ዓለም የሰላም “ታላቅ ስጦታ” ከእግዚአብሔር ለመለመን የጸሎት እና የንስሐ ቀን አውጀው ነበር። የጸሎት መርሐ ግብሩ እ.አ.አ ከመስከረም 7/2013 ዓ.ም የሰላም ንግሥት በሆነችው በልደታ ማርያም በዓል ዋዜ ምሽት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተካሄደ ሲሆን የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ባደረጉት ስብከት ሁሉም ሰው “የእርቅና የሰላም ገንቢዎች” እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ጦርነት እብደት ነው።
በሌሎች ሁለት አጋጣሚዎች የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰዎችን ለመካከለኛው ምስራቅ እንዲጸልዩ ምዕመናንን ጋብዘው የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ. በጥቅምት 27 ቀን 2023 ዓ.ም በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ከሃያ ቀናት በኋላ በወቅቱ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዩሐንስ 23ኛ በላቲን ቋንቋ "Pacem in terris" (ሰላም በምድር ላይ ይሁን) ተብሎ የሚጠራው ጳጳሳዊ መልእክት ይፋ የሆነበት 60ኛ አመት በቫቲካን በተከበረበት ወቅት የአንድ ሰአት የጸሎት እና የቅዱስ ቁርባን ስግደት ቀን በቫቲካን ባሲሊካ ተካሄዷል። "ይህ የጨለማ ሰዓት ነው እናቴ" ሲሉ ጳጳሱ የተማጽኖ ጥሪ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አቅርበው ነበር።እናም በዚህ የጨለማ ሰአት በሚያንጸባርቁ አይኖችሽ ውስጥ ጠልቀን ገብተን ራሳችንን ለልብሽ አደራ እንሰጣለን፣ ስለዚህም የሰው ልጅ "ሞትን የሚዘራውንና የወደፊቱን የሚሽር የጦርነት ሞኝነት እንዲክድ" እንማጸንሻለን በማለት መጸለያቸው ይታወሳል። ከአንድ ዓመት በኋላ፣ እ.አ.አ በጥቅምት 6/2024 ዓ.ም የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኘውን ዐብይ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተው ለሰላም ተማጽነዋል። ከዚህም በላይ ግጭቱ ከተጀመረ ልክ አንድ ዓመት በሆነው በሚቀጥለው ቀን ልዩ የጸሎት እና የጾም ቀን አወጀው ነበር።
የሰላም ንግሥት ለማርያም ጥሪ
የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.አ.አ በሕዳር 2/2022 ዓ.ም የዐብይ ጾም ከመጀመሩ በፊት ለዩክሬይን ሰላም እንድንጸልይ አሳስበው የነበረ ሲሆን ሞስኮ በኪየቭ ላይ ጥቃት ከሰነዘረች ከሳምንት በኋላ ጳጳሱ የሰላም ንግሥት የሆነችው እምቤታችን ድንግል ማርያም “ዓለምን ከጦርነት ሞኝነት እንድትጠብቅ” መማጸናቸው ይታወሳል። ከአመት በኋላም ቢሆን የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዩክሬን እና ሩሲያ ግጭቱን እንዲያቆሙ ለድንግል ማርያም ንፁህ ልብ በአደራ መስጠታቸው ይታወሳል።
የተረጋጋ ሰላም በፍትህ ላይ የተመሰረተ ነው።
በዓለም ዙሪያ እርቅን የሚያበረታቱ ጅምሮች በቅዱስ ጴጥሮስ የቅርብ ተተኪዎችም ተበረታተዋል፡ ለምሳሌ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እየተባባሰ ባለበት ወቅት በነዲክቶስ 16ኛ “የሰላምን ስጦታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምኑ” በማለት ልዩ የጸሎትና የንስሐ ቀን እ.አ.አ በሐምሌ 23/2006 ዓ.ም. ሰይመው እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በመጨረሻም በኒውዮርክ ከተማ እ.አ.አ በመስከረም 11 ቀን መንትዮቹ ሕንጻዎች ላይ ጥቃት ከተፈጸመ ከሦስት ወራት በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ ታኅሣሥ 14 ቀን 2001 ዓ.ም የታወጀው የጾም እና የጸሎት ቀን የጋራ ትውስታዎቻችን ናቸው፦ ዓላማው “በፍትሕ ላይ የተመሰረተ የተረጋጋ ሰላም ለዓለም እንዲሰጥ አምላክን አጥብቆ መለመን” ነው።