ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “እራሳችንን ለግጭት እና ለጦር መሣሪያዎች ማንበርከክ የለብንም” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያቸው ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው በሥፍራው ለተገኙት ምዕመናን የፍልሰታ ማርያም በዓልን በማስመልከት ንግግር ባሰሙበት ወቅት፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰላምን እንድታማልደን ጸሎታቸውን አድርሰው፥ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጆቿ በተለይም በሕፃናት እና በአቅመ ደካሞች ላይ በሚደርስ መከራ ትሰቃያለች” ብለው፥ “ባለፉት ዘመናት በሙሉ ለተቸገሩት ሰዎች ያላትን ቅርበት በመልዕክቶቿ እና በግልጸቷ አረጋግጣለች” ብለዋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ፥ “በዓለም ታይቶ የማያውቅ ደም አፋሳሽ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት” በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1950 ዓ. ም. የፍልሰታ ማርያም ዶግማ ማወጃቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በመልዕክታቸውም፥ “በእመቤታችን ማርያም ክቡር ምሳሌ ላይ የሚያሰላስሉት በሙሉ በሰው ሕይወት ዋጋ ይበልጥ እርግጠኞች ይሆናሉ ብለን ተስፋ የምናደርግበት ምክንያት አለ” ካሉ በኋላ በመቀጠልም ዓለም በጦርነት ምክንያት የሚታረደውን የሰውን ሥጋ ዳግም እንደማያይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተናገሯቸው ቃላት ዛሬም ጠቃሚ ሆነው ይቀጥላሉ በማለት አበክረው ተናግረው፥ የሰው ልጆች በሙሉ በዓለም ላይ እየተስፋፋ በመጣ ዓመፅ መካከል አቅመ ቢስነት እንደሚሰማቸው እና በአመጹ መብዛት ምክንያት ማንኛውም ዓይነት የሰው ልጅ የሰላም ጥረት ተቀባይነትን ወደማያገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው ማጠቃለያ ባቀረቡት ማሳሰቢያ፥ “ነገር ግን ተስፋ ማጣት የለብንም” ብለው፥ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ኃጢአት እና ከሚደርስባቸው ግፎች በሙሉ እንደሚበልጥ ተናግረው፥ “እራሳችንን ለግጭት እና ለጦር መሣሪያዎች የበላይነት ማንበርከክ የለብንም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላካችን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር እንደሚረዳን እናውቃለን፤ የሰላሙን መንገድ እንደገና ማግኘት የምንችለውም በእግዚአብሔር ምሕረት ብቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።