MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ተስፋ በምድራዊ ጉዟችን ላይ ወሳኝ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለፓን አፍሪካ ካቶሊካዊ የሥነ-መለኮት እና ሐዋርያዊ አውታረ መረብ ቡድን ሦስተኛ ጉባኤ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ ቡድኑ የአህጉሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተስፋ እንዲመለከት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የፓን አፍሪካ ካቶሊካዊ የሥነ-መለኮት እና ሐዋርያዊ አውታረ መረብ (PACTPAN) ሦስተኛ ጉባኤን ምክንያት በማድረግ ቡድኑ ለሚያደርገው ትጋት የተሞላበት ጥረት አድናቆታቸውን በመግለጽ፥ “አፍሪካ ውስጥ በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ለማሰላሰል የተሰበሰቡትን በሙሉ በጸሎት በማስታወስ የቪዲዮ መልዕክት ልከዋል።

በጉዟችን ላይ ተስፋ ወሳኝ ነው!

በሁለተኛው ጉባኤ ላይ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ እምነት አስፈላጊነት የተናገሩትን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ትኩረታቸውን በኢዮቤልዩ ዓመት ብርሃን ላይ በማድረግ ተስፋ ወደሚለው ሥነ-መለኮታዊ በጎነት ቀይረው፥ “ምናልባት በጎነት አንዳንድ ጊዜ ለእምነት እና ለበጎ አድራጎት የበለጠ ዕውቅናን ይሰጥ ይሆናል” ብለው፥ “ሆኖም ተስፋ በምድራዊ ጉዞአችን ላይ ወሳኝ ሚና አለው” ሲሉ አበክረው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ተስፋ ሌሎችን ሁለት በጎነቶች እነርሱም እምነትን እና ፍቅርን ያገናኛል” ብለው፥ በገነት ውስጥ ደስታን እንድንመኝ የሚያደርግ በጎነት እንደሆነ አስረድተው፥ እሱም በተራው በሕይወታችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ የሚያነሳሳን እና የሚደግፈን ነው ብለዋል።

የሚለያዩ ሳይሆን አንድ ናቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የአፍሪካ አኅጉርም በዓለም ዙሪያ እንዳሉት ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የራሱ ልዩ ፈተናዎች እንዳሉበት አመላክተው፥ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም የተስፋ ብርሃን የመሆን ሚና እንዳላት አጽንኦት ሰጥተዋል።

“በአፍሪካ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሆነን በተስፋ አብረን መጓዝ” የሚለውን የጉባኤውን ጭብጥ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር ጋር የግል ዝምድናን እንድንመሠርት በቀረበልን ጥሪ ላይ በማሰላሰል፥ ሁላችንም እንደ ወንድም እና እህት አንድ ላይ መሆናችንን ጠቁመዋል።

በመሆኑም “እርስ በርስ የመተሳሰብ ኃላፊነት አለብን” ብለው፥ በተለይ በችግሮች መካከል ወደ ፊት ለመራመድ የመጀመሪያውን የድጋፍ፣ የፍቅር እና የማበረታቻ ዕርዳታን ለማግኘት የታሰበው ቤተሰብ መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይህን በማስታወስ፥ የፓን አፍሪካ ካቶሊካዊ የሥነ-መለኮት እና ሐዋርያዊ አውታረ መረብ አባላት “PACTAN” በተለያዩ አገራት ውስጥ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ያሉ ቤተሰቦችን መገንባት እንዲቀጥሉ አሳስበው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለሆኑት በሙሉ እንዲሁም ለሰፊው ኅብረተሰብ በተለይም ወደ ጎን ለተባሉት ድጋፍ እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቪዲዮ መልዕክታቸውን መደምደሚያ፥ በሥነ-መለኮታዊ እና ሐዋርያዊ ሥራቸው አንድ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ቡድኑን አስታውሰዋል፥ “የምናምነውን በተግባር መኖር አለብን” ሲሉ አሳስበው፥ የሰዎችን ልብ እና አእምሮ ለእግዚአብሔር እውነት እና ፍቅር በቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች አማካይነት እንዴት መክፈት እንደሚቻል የሚያሳዩ ሐዋርያዊ ፕሮግራሞችን ለግሠውላቸዋል።

የፓን አፍሪካ ካቶሊካዊ የሥነ-መለኮት እና ሐዋርያዊ አውታረ መረብ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2019 ዓ. ም. በይፋ የተመሠረተው የፓን አፍሪካ ካቶሊካዊ የሥነ-መለኮት እና ሐዋርያዊ አውታረ መረብ (PACTPAN) ለሁሉም የአፍሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና የሐዋርያዊ አገልግሎት መሪዎች ክፍት የሆነ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ለአፍሪካ ካቶሊካዊ ምሁራን፣ ለሐዋርያዊ አገልግሎት መሪዎች፣ አፍሪካ ውስጥ ባሉት ከተሞች እና መንደሮች ውስጥ ለሚገኙት ግንባር ቀደም ቤተ ክርስቲያን ተዋማዮች እና ሠራተኞች ሁለ-ገብ ምርምር ቋሚ ኤጀንሲ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በተጨማሪም አባላቱ ድምጽ የሌላቸውን ለማገልገል እንዲተጉ የሚያበረታታ ድርጅት ነው።

06 Aug 2025, 17:48