MAP

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ‘ሰላም የሚጀምረው ከምንናገረውና ከምንሠራው ነገር ነው’ ማለታቸው ተገለጸ!

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሰሜን አሜሪካ ቪላኖቫ በመባል በሚታወቀው ግዛት ውስጥ ለሚኖሩ የቅዱስ አጎስጢኖስ ማሕበር አባላት የመንፈሳዊ አባታቸውን አመታዊ በዓል ምክንያት በማድረግ  የቪዲዮ መልእክት መላካቸው የተገለጸ ሲሆን ሁሉም ሰው የእግዚአብሔርን አፍቃሪ ድምፅ እንዲያዳምጡ ጋብዘዋል ፣ ይህም ብቻውን ሰላምን ያመጣል ብለዋል ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በነሐሴ 22/2017 ዓ.ም የተከበረውን የቅዱስ አጎስጢኖስ አመታዊ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱስ አውግስጢኖስን የሜዳልያ ሽልማት በማግኘታቸው ምስጋናቸውን ለአሜሪካው የቪላኖቫ የቅዱስ ቶማስ ግዛት በቪዲዮ መልእክት ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመልእክታቸው፣ “የድሆች አባት” በመባል የሚታወቁት በቅዱስ ቶማስ ስም የሚጠራው ቁምስና ውስጥ የሚያገለግሉትን የቅዱስ አጎስጢኖስ ማሕበር አባላት ወንድሞች እና ለጳጳሳቸው ያላቸውን አድናቆት እና ክብር ገልጸዋል።

"እንደ ቅዱስ አውግስጢኖስ ማሕበር አባል ሆኜ መታወቄ ትልቅ ክብር ነው። የቅዱስ አውግስጢኖስ መንፈስ እና አስተምህሮት ባለውለታዬ ነው። ሕይወቶቻችሁ "ለቬሪታስ፣ ሁኒታስ፣ ካሪታስ" ("Veritas፣ Unitas፣ Caritas" የላቲን ሐረግ ሲሆን ትርጉሙም "እውነት፣ አንድነት እና ፍቅር" ማለት ነው። የቪላኖቫ ዩኒቨርሲቲ መሪ ቃል ነው፥ ዩኒቬርስቲው እነዚህን ዋና ዋና እሴቶች ከቅዱስ አውግስጢኖስ ካቶሊካዊ ቅርሶች ወርሷል። ሀረጉ እውነትን ለመፈለግ፣ ማህበረሰብን ለማሳደግ እና በጎ አድራጎት እና አገልግሎትን በትምህርት እና በእለት ተዕለት ሕይወት ለመለማመድ የዩኒቨርሲቲው የምያደርገውን ቁርጠኝነት ያሳያል) ለእነዚህ እሴቶች ጥልቅ ቁርጠኝነት ስላሳያችሁ ብዙ መንገዶችን ስለከፈታችሁ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ" ሲሉ ቅዱስነታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅዱስ አጎስጢኖስ ሕይወት ላይ ሲያሰላስሉ፣ የቅዱስ አውግስጢኖስ ጉዞ “እንደ ሕይወታችን በፈተና እና በስህተት የተሞላ ነበር” ብለዋል። ሆኖም በጸጋ፣ በእናቱ ሞኒካ ጸሎቶች እና በዙሪያው ባሉት ማህበረሰቦች ምስክርነት፣ “እረፍት ለሌለው ልቡ የሰላም መንገድ” አገኘ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የቅዱስ አውግስጢኖስ ምስክርነት እያንዳንዱ ክርስቲያን አምላክ የሰጣቸውን ስጦታዎች እንዲገነዘቡ እና “ለእግዚአብሔርና ለባልንጀራችን በፍቅር አገልግሎት” እንድናቀርብ እንደሚጋብዘን አስምረውበታል።

የፍቅር አገልግሎት ረጅም ትሩፋት

ከዚያም በ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ አባ ማቲው ካር እና አባ ጆን ሮሲተር ስደተኞችን በማገልገል ያደረጉትን ሚስዮናዊ ቅንዓት በማስታወስ በአሜሪካ ውስጥ ካሉት አንጋፋ የካቶሊክ ማህበረሰቦች አንዱ በሆነው በፊላደልፊያ ወደሚገኘው የቅዱስ አጎስጢኖስ ማሕበር መነኩሳት ሐሳባቸውን ያዞሩ ሲሆን ይኸው መንፈስ፣ “የፍቅር አገልግሎት ትሩፋትን እንድንቀጥል ዛሬ ይጠራናል” ብሏል።

“ኢየሱስ ባልንጀራችንን እንድንወድ በወንጌል አሳስቦናል” ሲሉ ጳጳሱ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን ሁሉም በክርስቶስ ዓይን እርስ በርስ እንዲተያዩ እና ማንነታችንን እንደገና እንድናገኝ “በእሱ ያሉ እህቶች እና ወንድሞች” በማገልገል መኖር ይኖርብናል በማለት አሳስበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቅዱስ አጎስጢኖስን ቃል በመጥቀስ—“ልባችሁን በጆሮአችሁ ውስጥ አታድርጉ፣ ነገር ግን ጆሮአችሁ በልባችሁ ውስጥ ይሁን” (ይህ ማለት ከአምስቱ የስሜት ሕዋሳቶቻችን መካከል አንዱ በሆነው በጆሮ ብቻ ከመስማት ይልቅ፣ በእውነተኛ ማስተዋልና ርኅራኄ ማዳመጥ ማለት ነው። እውነተኛ ማዳመጥ ሌላ ሰው የሚያስተላልፈውን በትክክል ለመረዳት የልብን ስሜታዊ፣ መንፈሳዊ እና አእምሯዊ ገጽታዎች ማሳተፍን፣ ከቃላት አልፈው ስሜታቸውን፣ ሀሳባቸውን እና ውስጣዊ እውነትን መረዳትን እንደሚጨምር አጽንኦት ይሰጣል። በአጠቃላይ ምንም እንኳን ልብ ጆሮ ባይኖረውም በልብ ጆሮ (ልብ ብሎ) ማዳመጥ የሚለውን ትርጉም ይሰጣል)

በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ የቅዱስ አጎስጢኖስን ቤተሰብ የማዳመጥ መንፈስን እንዲቀበሉ ጋብዘዋል። “ከመናገራችን በፊት መደማመጥ አለብን” በማለት በሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ጥሪው መንፈስ ቅዱስን እንድንሰማ፣ እርስ በርሳችን እና በተለይም የድሆችን ድምፅ እንድንሰማ ነው የተጠራነው ብለዋል።

ሰላም የሚያመጣውን የእግዚአብሔርን አፍቃሪ ድምፅ ለመስማት ሁሉም የዓለምን ጫጫታ እና መለያየት እንዲያጣሩ አበረታቷል። “ያን የሚያረጋጋ ድምጽ ስንሰማ፣ በእርሱ አንድ ለመሆን በምንጥርበት ጊዜ ለአለም ልናካፍለው እንችላለን” ብሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “እግዚአብሔር ሁላችሁንም ይባርካችሁ፣ ረፍት ለሌለው ልባችን ሰላምን ያምጣን፣ እናም በአእምሮ እና በልባችሁ፣ በእግዚአብሔር ላይ አሳብ ያለው የፍቅር ማህበረሰብ መገንባት እንድትቀጥሉ እርሱ ይርዳችሁ” በማለት የቅዱስ አውግስጢኖስ ቤተሰብን የመልካም ምክር እናት ለሆነችው ለድንግል ማርያም በአደራ ሰጥተዋል።

 

29 Aug 2025, 11:33