MAP

ITALY-VATICAN-RELIGION-POPE-CASTEL GANDOLFO-ANGELUS ITALY-VATICAN-RELIGION-POPE-CASTEL GANDOLFO-ANGELUS  (AFP or licensors)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት እና በጋዛ ያለው ረሃብ እንዲያበቃ ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅድስት መንበርን ዲፕሎማሲ በመከተል በዩክሬን እና በጋዛ የሚካሄዱ ጦርነቶች በውይይት ሊፈቱ ይገባል ሲሉ አሳሰቡ፡፡ ቅዱስነታቸው ይህን ለጋዜጠኞች የተናገሩት በካስቴል ጋዶልፎ ወደሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያቸው እስከ መጭው ማክሰኛ ነሐሴ 13/2017 ዓ. ም. ድረስ ለዕረፍት በተመለሱበት ወቅት ሲሆን፥ በቆይታቸው ወቅት የሚከበሩ በዓላትንም እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለጋዘጤኞቹ እንደተናገሩት፤ በዩክሬን ስለሚደረሰው የተኩስ አቁም እና የሰላም ስምምነት፣ ስለ ጋዛ የሰብዓዊ ቀውስ እና ረሃብ መፍትሄ እና እስራኤላውያን ታጋቾችን ስለመፍታት በማስመልከት ተናግረው፥ እነዚህ በጦርነት ሊፈቱ የማይችሉ ጉዳዮች በቅድስት መንበር የተረጋጋ ዲፕሎማሲ መፍታት የሚቻል መሆኑን ረቡዕ ነሐሴ 7/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በካስቴል ጋንዶልፎ ወደሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሲደርሱ እንደሆነ ተገልጿል።

ዘወትር ውይይትን እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን መፈለግ ይገባል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓርብ ነሐሴ 9/2017 ዓ. ም. በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መካከል ከሚደረገው ስብሰባ ምን እንደሚጠብቁ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “ብጥብጥን እና የብዙዎች ሞትን ለማስቀረት ዘወትር የተኩስ አቁም ስምምነትን መፈለግ አለብን” ብለው፥ መሪዎቹ ወደ ስምምነት ሊደርሱ የሚችሉበትን መንገድ ተስፋ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበው፥ “ምክንያቱም ከዚህ ረጅም ጊዜ በኋላ የጦርነቱ ዓላማ ምን እንደሆነ ስለማይታወቅ በውይይት እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጦርነት የሚቆምበትን መንገድ መፈለግ አለብን” ብለዋል፡፡

የጋዛ ሕዝብ ከገዛ መሬቱ ሊባረር የሚችልበት ዕድል የሚሳስባቸው እንደሆነ የተጠየቁት ቅዱስነታቸው፥ “በእርግጥ እጅግ ያሳስበኛል” ካሉ በኋላ ሰብዓዊ ቀውሱ መፈታት እንዳለበት፥ የሽብር ተግባር እና ዓመፅ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት እንደሚታወቅ ተናግረው፥ በአደጋው ለሞቱት ምሕረትን በመለመን፣ የታገቱት ነፃ ሊወጡ እንደሚገባ ተማጽነው በረሃብ ምክንያት የሚሞቱትን በርካታ ሰዎች ማሰብ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

በጦርነት የማይፈቱ ችግሮች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመጨረሻም፥ እነዚህን እና ሌሎች ግጭቶችን ለማስቆም ቅድስት መንበር ምን እየሠራች እንደምትገኝ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡- “ቅድስት መንበር ጦርነቶችን ልታስቆም የምትችለው በተረጋጋ ዲፕሎማሲ ነው” ብለው መፍትሄዎችን በውይይት እንዲፈልጉ በመጋበዝ ላይ እንደምትገኝ ከገለጹ በኋላ ችግሮች በጦርነት ሊፈቱ እንደማይችሉም አስረድተዋል።


እግዚአብሔር ለሕዝቦች በሙሉ ሰላምን ይስጥ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ረቡዕ ነሐሴ 7/2017 ዓ. ም. ማለዳ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሳምንታዊ ጠቅላላ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት ከፖላንድ ለመጡት ነጋዲያን ሰላምታቸውን ካቀረቡ በኋላ በጦርነት እና በዓመፅ ለሚሰቃዩት ሰዎች ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ፖላንዳዊውን ፍራንችስካዊ ቅዱስ ማክስሚሊያን ማርያ ኮልቤን በመጥቀስ፥ ቅዱስ ማክስሚሊያን ኮልቤ በጀርመን ኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በረሃብ እንዲሞት የተፈረደበትን የቤተሰብ አባት ተክቶ ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በካስቴል ጋንዶልፎ የሚያሳርጉት ቅዳሴ እና የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በካስቴል ጋዶልፎ መኖሪያቸው በሚያሳልፉት ሁለተኛ ዙር የበጋ ዕረፍት ወቅት በሚከበሩ በዓላት ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፤ ዓርብ ነሐሴ 9/2017 ዓ. ም. የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል በቅዱስ ቶማስ ቁምስና በሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ካከበሩ በኋላ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በሐዋርያዊ ሕንጻ መግቢያ ላይ የሚቀርበውን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ይመራሉ።


ከመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት በኋላ ማዕድ ይጋራሉ

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም እሑድ ነሐሴ 11/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ በአልባኖ ሀገረ ስብከት በሚገኝ በቅድስት ማርያ ዴላ ሮቶንዳ ቤተ መቅደስ ውስጥ ከድሃ ቤተሰቦች ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ ቀጥለውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በካስቴል ጋንዶልፎ ውስጥ በፒያሳ ዴላ ሊበርታ የሚቀርበውን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ይመራሉ። በመጨረሻም በ “ካሪታስ” የበጎ አድራጎት ድርጅት ከሚታገዙ ድሃ ቤተሰቦች ጋር በጳጳሳዊ መኖሪያ ግቢ ውስጥ በተዘጋጀላቸውን የምሳ ግብዣ ላይ ያዘጋጀውን ምሳ ይካፈላሉ።

14 Aug 2025, 16:43