ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በሕንድ የመጀመሪያው ሊጧናዊ ካኅን 400ኛ ዓመት መታሰቢያን አከበሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የመጀመሪያው ሊጧናዊ የኢየሱሳውያን ማኅበር አባል አባ አንድሪውስ ሩዳሚና ወደ ሕንድ የገቡበትን 400ኛ ዓመት መታሰቢያን በማስመልከት በሕንድ ለጎዋ እና ዳማን ሀገረ ስብከቶች የቴሌግራም መልዕክት ልከዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በፈረሙት ደብዳቤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዕለቱን ለማስታወስ በ “ኦልድ” ጎዋ በሚገኘው በሴ ካቴድራል ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና ተጋባዥ እንግዶች በሙሉ መልካም ምኞታቸውን ልከዋል።
ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው የአባ አንድሪውስ ሩዳሚና ሚስዮናዊነት እና ጠንካራ የካቶሊክ እምነት በአሁኑ ወቅት በሊጧኒያ በግልጽ እንደሚታይ ገልጸው፥ ለምስክርነታቸው ምስጋናቸውን ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ከተሰበሰቡት ጋር መተባበራቸውን ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “መታሰቢያ በዓሉ የአባ አንድሪውስ ሩዳሚና ታላቅ ልግስና እና ድፍረት፥ ወንጌልን ወደ ሁሉ ሥፍራ ለማዳረስ በዘመናችን ያሉ ብዙ የወንጌል አገልግሎቶችን በተመሳሳይ ትዕግስት እና ብልሃት ለማበርከት እንዲያግዛቸው” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የአባ አንድሪውስ ሩዳሚና ሚሲዮናዊ ቅንዓት እና አስደናቂ የውይይት እና የባሕል ውህደት ቅርስ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በሚገኙ ቁምስናዎች እና አብያተ ክርስቲያናት መካከል የወንድማዊ ስምምነት፣ የእርቅ እና የመግባባት አርአያ ሆኖ ሁሉን እንደሚያገለግል እና በክርስቲያኖች መካከል በመደረግ ላይ የሚገኘውን የጋራ ውይይት እንደሚበረታታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በተጨማሪም “መታሰቢያ በዓሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የደስታ እና የሰላም ቃል ኪዳን እንዲሆን” በማለት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን በመላክ የቴሌግራም መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
የመጀመሪያ አዲስ የወንጌል አገልጋይ
አባ አንድሪውስ ሩዳሚና በ29 ዓመት ዕድሜው ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1625 ዓ. ም. ከ11 ፖርቱጋላዊ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ወደ ሕንድ ለመድረስ 6,000 ማይል አደገኛ ጉዞ ማድረጉ ሲነገር፥ የኢየሱሳውያን ማኅበር መሥራች የቅዱስ ኢግናጢዮስ ተከታይ የሆኑት አባ አንድሪውስ ሩዳሚና ሰፊውን የሕንድ ግዛት ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡ መሆናቸው ታውቋል።
አባ አንድሪውስ ሩዳሚና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1626 ዓ. ም. በወባ በሽታ ተይዘው ወደ ቻይና ከመዛወራቸው ቀደም ብሎ ሕንድ ውስጥ እንደኖሩ እና ቻይና ውስጥ ለአምስት ዓመታት ከኖሩ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል። በትውልድ አገራቸው ሊጧኒያ ውስጥ የመታሰቢያ ድንጋይ የተቀመጠው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2015 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል።