MAP

በጃፓን ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪየቦምብ ጥቃት የተፈፀመበት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ በጃፓን ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪየቦምብ ጥቃት የተፈፀመበት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ  (ANSA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሂሮሺማ ጥቃት መታሰቢያ የሰላም ጥሪ ሊሆን እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በጃፓኗ ከተማ ሂሮሺማ የቦምብ ጥቃት የተፈፀመበትን 80ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ሰኞ ሐምሌ 29/2017 ዓ. ም. መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የገባውን ቃል እንዲያድስ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ውህደታቸውን እንድንከባከብ የተጠራንበትን የጋራ ሰብዓዊነታችን እና የፍጥረትን ክብር ይሰጣሉ” በማለት ለሄሮሺማ ጳጳስ አቡነ አሌክሲስ ሺራማ ያስተላለፉትን መልዕክት፥ በአገሪቱ የሚገኙት ሐዋርያዊ እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንችስኮ ኤስካላንቴ ሞሊና በሂሮሺማ ስለ ሰላም በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ በንባብ አስምተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ ጦር በጃፓን ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ በፈጸመው የኒውክሌር ቦምብ ጥቃት ከ150,000 እስከ 246,000 የሚደርሱ ሰዎች የተገደሉበት 80ኛ ዓመት መታሰቢያን በማስመልከት በላኩት መልዕክት፥ “እነዚህ ሁለቱ ከተሞች ኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ሊያደርሱ የሚችሉትን ከባድ አሰቃቂ ጥፋቶችን የሚያስታውሱ ናቸው” ብለዋል።

በጃፓን ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የቦምብ ጥቃት የተፈፀመበት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ
በጃፓን ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የቦምብ ጥቃት የተፈፀመበት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ   (AFP or licensors)

ጥቃት ተፈጸመባቸው በሕይወት ለተረፉት ለሂባኩሻ ስዎች ያላቸውን ክብር ገልጸው፥ “ታሪካቸው ከጦርነት የጸዳ አስተማማኝ እና ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት ለሁላችንም ወቅታዊ ጥሪ ነው” ብለዋል።

ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ጦርነት ለሰው ልጆች ምንጊዜም ሽንፈት ነው” በማለት ደጋግመው ያቀረቡትን ጥሪ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በተለይም ኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች በቃላት ሊገለጽ የማይችል ጥፋት የማድረስ ኃይል እንዳላቸው አስረድተው፥ እውነተኛ ሰላም የጦር መሣሪያን በድፍረት ማስቀመጥን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፥ “ኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች አንድነታቸውን እንድንከባከብ የተጠራንበትን የጋራ ሰብዓዊነታችን እና የፍጥረትን ክብር ይጥሳሉ” ብለዋል። 

በጋራ ጥፋት ላይ የተመሠረተ ሐሰተኛ የጸጥታ ሁኔታ

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመጥቀስ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ “ዓለም አቀፋዊ ውጥረቶች እና ግጭቶች እየጨመሩ በሄዱበት ወቅት ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የማስታወሻ ምልክት ሆነው የቆዩ በመሆናቸው በጋራ ውድመት ላይ የተመሠረተውን ሐሰተኛ የጸጥታ ሁኔታ መቀበል የለብንም”  በማለት ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም “ይልቁንም በፍትህ፣ በወንድማማችነት እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ዓለም አቀፋዊ ሥነ-ምግባርን መፍጠር አለብን” ብለዋል።

ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረበ ጥሪ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ መታሰቢያ ክብረ በዓሉ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለመላው ሰብዓዊ ቤተሰባች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የገባውን ቃል እንዲያድስ፣ የጦር መሣሪያ ትጥቅ የሌለበት እና የታጠቁትንም የሚያስፈታ የሰላም ጥሪ እንዲሆን በጸሎት ጠይቀዋል።

 

06 Aug 2025, 17:23