MAP

ር.ሊ.ጳ. ሊዮ በስብከታቸው ጌታ በእርጋታ የነፍሳችሁን መስኮት ያንኳኳል ማለታቸው ተገለጸ!

የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች የኢዩቤሊዩ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ በሐምሌ 27/2017 ዓ.ም በሮም ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ቶር ቬርጋታ በሚባለው ሥፍራ መከናወኑ የሚታወቅ ሲሆን በአጠቃላይ ከአንድ ሚልዮን በላይ ምዕመናን በሥፍራው ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴ ታድመዋል፣ 450 በላይ ጳጳሳት ከ7ሺ በላይ ካህናት፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ተሳትፈዋል። መስዋዕተ ቅዳሴው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ተመርቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባደረጉት ስብከት ወጣቶች ታላላቅ ነገሮች  እንዲመኙ፣ ሁሉንም ሰው በእምነት ምስክርነታቸው አንዲያበሩ ጥሪ ያደረጉ ሲሆን የሕይወት ሙላት በምንሰበስባቸው ነገሮች ላይ የተመሰረተ አይደለም፣ ነገር ግን “በደስታ በተቀበልነውና ለሌሎች በምናካፍለው” የእግዚአብሔር ፍቅር በክርስቶስ በተገለጡ ነገሮች ነው እንጂ። የልብን ጥማት የሚያረካ እና ለእረፍት ማጣት መልስ የሚሰጥ እርሱ ነው ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

"የትም ብትሆኑ ታላቅ ነገር የሆነውን ቅድስናን ተመኙ። ብዙም አትቀመጡ። ያኔ የወንጌል ብርሃን በየዕለቱ በአንተና በዙሪያችሁ እያደገ ሲሄድ ታያላችሁ" ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በተቻለ መጠን ከወጣቶች ጋር ለመቀራረብ እንደሚፈልጉ በቶር ቬርጋታ በነበራቸው ቆይታ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

እንደ የዝግጅቱ አዘጋጅ ባለሥልጣናት ከሆነ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በሮም ዳርቻ ተሰብስበው የነበረ ሲሆን 20 ካርዲናሎች፣ በግምት 450 የሚጠጉ ጳጳሳትን ጨምሮ ወደ 7,000 የሚጠጉ ካህናት—ለወጣቶች ኢዮቤልዩ ቅዳሴ የተሰበሰቡ ሲሆን ለዚህም ጋዜጠኞችን፣ ፎቶግራፍ አንሺዎችን፣ የካሜራ ባለሙያዎችን እና የቪዲዮ ቀራጮችን ጨምሮ 850 የሚዲያ ሠራተኞች ተካፍለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መድረክ ላይ እንደደረሱ ለቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ከመዘጋጀታቸው በፊት ሰላምታ ለተሳታፊዎች ያቀረቡ ሲሆን "እንደምን አደራችሁ፣ ሁላችሁም መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!" በማለት በሰላምታ ጀምረዋል፣ በመቀጠልም የእግዚአብሔር ቡራኬ በሁሉም ላይ ይሆን ዘንድ የተማጸኑ ሲሆን "ክርስቶስ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ እንደሚገኘ አምነን መስዋዕተ ቅዳሴ በምናከናውንበት ወቅት "ለእያንዳንዳችን በእውነት የማይረሳ ክስተት" እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፣ "እንደ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ አንድ ላይ ስንሆን፣ እርሱን በሚገባ እንከተላለን፣ አብረን እንሄዳለን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እንኖራለን" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ወደ ላይ ተመልከቱ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጣሊያንኛ፣ በከፊል በስፓኒሽ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ባቀረቡት ስብከታቸው ትናንት ምሽት ስለ ወጣት ትውልድ ጭንቀት፣ አለመረጋጋት እና ጥርጣሬ ከተናገሩት ሦስት ወጣቶች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡ በኋላ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አጠር አድርገው የወጣቶችን ሚና በመግለጽ ሦስት ጥያቄዎችን አቅርበዋል። "በእርግጥ ደስታ ምንድን ነው? የሕይወት ትክክለኛ ትርጉም ምንድን ነው? ከረጋ የከንቱነት መንፈስ፣ የመሰልቸት እና የግድዬለሽነት መንፈስ ነፃ የሚያወጣን ምንድን ነው?" ሲሉ ቅዱስነታቸው ጥያቄ ያነሱ ሲሆን እናም ባለፉት የኢዮቤልዩ ቀናት ሁሉም ሰው ያጋጠሙትን “ብዙ የሚያምሩ ገጠመኞች” ጠቅለል አድርጎው ቅዱስነታቸው አቅርበዋል፣ መልስ ሰጥተዋል፡- “ከተለያዩ የአለም ክፍሎች ካሉ እኩዮቻችሁ ጋር ከተለያዩ ባህሎች ጋር ተገናኝታችኋል። እውቀት ተለዋውጣችኋል፣ የምትጠብቁትን ነገሮች ተካፍላችኋል፣ እናም ከከተማዋ ውስጥ በኪነጥበብ፣ በሙዚቃ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በስፖርት መስክ ተሰማርታችኋል።ከዚያም ቺርኮስ ማክስሙስ በተሰኘው ሥፍራ ወደ ምስጢረ ንስሐ በመቅረብ እና የሕሊና ምርመራ በማድረግ የእግዚአብሔርን የንስሃ ምህረት ጠይቃችኋል ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች የኢዩቤሊዩ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ
የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች የኢዩቤሊዩ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ   (@Vatican Media)

መልሱ በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ላይ ነው የሚገኘው ያሉት ቅዱስነታቸው፡- “የሕይወታችን ሙላት በምንሰበስበው ነገር ላይ የተመካ አይደለም” ያሉት ሊዮ አሥራ አራተኛ “በእኛ ንብረት ላይ እንኳ የተመካ አይደለም” ብሏል። ይልቁንም የደስታችን መሰረት “በደስታ በተቀበልነው እና ለሌሎች በምንካፍለው” በክርስቶስ ፍቅር ውስጥ ነው የሚገኘው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ ለወጣቶች የኢዮቤልዩ ቅዳሴ ማብቂያ ላይ፣ በቶር ቬርጋታ ከሚገኙት ሚሊዮን ወጣት ወንዶችና ሴቶች ጋር በመሆን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አከናውነዋል።

መግዛት፣ ማጠራቀም፣ መብላት በቂ አይደለም። ዓይኖቻችንን ቀና ማድረግ፣ ወደ ላይ ያሉትን "ከላይ ያሉትን ነገሮች" መመልከት አለብን፣ በዓለም ካሉት እውነታዎች መካከል፣ ከእግዚአብሔርና ከወንድሞቻችን ጋር በበጎ አድራጎት ተግባር እንድንተሳሰር በሚያገለግል መጠን ብቻ፣ በውስጣችን “የዋህነትን፣ በጎነትን፣ ትሕትናን፣ ይቅርታን እና ሰላምን” እንደ ክርስቶስ ማሳደግ ይኖርብናል፣ በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ “በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍረንም” የሚለውን ምን ማለት እንደሆነ የበለጠ እንረዳለን። ውድ ወጣቶች ተስፋችን ኢየሱስ ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ኢየሱስ ሕይወታችንን ይለውጣል

“ሕልውናችንን የሚለውጠው ከትንሣኤው ክርስቶስ ጋር ያለው “ግንኙነት” ነው በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ  የተናገሩ ሲሆን ከመጀመሪያው ንባብ ከመጽሐፈ መክበብ ተወስዶ በተነበበው ንባብ በመነሳት “ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፥ ሁሉ ከንቱ ነው" (መ. መክብብ 1፡2) በማለት ያስጠነቅቃል፣ እናም እያንዳንዱ ሰው ያከማቸውን ትቶ “የሚያልፉትን ነገሮች ፍጻሜ” ማስታወስ ይኖርበታል ያሉ ሲሆን በተመሳሳይም መዝሙር 90 ላይ የተጠቀሰውን በማስታወስ “የበቀለውን ሣር አምሳል ይሰጠናል፤ ማለዳ ያብባል” ከዚያም “ሲመሽም ይጠወልጋል፣ ይደርቅማል" በማለት በእለቱ ሥርዓተ አምልኮ ላይ የተነበቡት ምንባባት "ሁለት ጠንካራ ማሳሰቢያዎች ይሰጡናል፣ ምናልባትም ትንሽ አስደንጋጭ ነገር ሊመስለን ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን ሊያስፈሩን አይገባም" ሲሉ ቅዱስነታቸው አበረታተዋል፥ ምክንያቱም "የሚናገሩን ስለሰው ልጅ ደካማነት ነው፣ በመሠረቱ እኛን ድንቅ ፍጥረት አድርጎ የመቁጠር አካል" ነው ብለዋል።

የሰው ልጅ ሕልውና ያለማቋረጥ በፍቅር ይታደሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሕይወታችን የፍቅር ዳግም መወለድ መሆኑን ለማብራራት እንደገና ሐሳባቸውን ወደ ተፈጥሮ ዘወር ያደረጉ ሲሆን  እንደ ሜዳ “ከቀጭኑ፣ ከተጋላጭ ግንድ፣ ለመድረቅ፣ ለመታጠፍ፣ ለመሰባበር የተዘጋጀ፣ ነገር ግን በአዲስ ግንድ እንደሚታደስ እኛም በእርሱ ፍቅር እንታደሳለን" ብለዋል።

"የተፈጠርነው ለዚህ ነው፣ ሁሉም ነገር የሚገመትበት እና የሚስተካከልበት ህይወት ሳይሆን በየጊዜው እራሱን በፍቅር ለሚያዳብር ህላዌ ነው። እናም ማንም የተፈጠረ እውነታ ሊሰጠን የማይችለውን 'የበለጠ' ነገርን ያለማቋረጥ እንመኛለን። በዚህ ዓለም ውስጥ ምንም ዓይነት መጠጥ ሊያረካው የማይችል በጣም ታላቅ እና የሚቃጠል ጥማት ይሰማናል። ይህ ሲያጋጥመን ልባችንን በማታለል ውጤታማ ባልሆኑ ተተኪ ነገሮች ለማርካት አንሞክር! ይልቁኑ ልባችንን እናዳምጠው"!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች የኢዩቤሊዩ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ማጠቃለያ ላይ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች የኢዩቤሊዩ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ማጠቃለያ ላይ   (@Vatican Media)

የልብን ጥማት የሚያረካ እግዚአብሔር ብቻ ነው

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጠቅለል ባለ መልኩ እንደገለጹት የልብ ጥማት በእግዚአብሔር ብቻ ነው የሚረካው፣ ቅዱስ አውግስጢኖስ "የተስፋችን ነገር" "ምድር" ወይም "ከምድር የሚወጣ ነገር እንደ ወርቅ፣ ብር፣ ዛፍ፣ አዝመራ፣ ውሃ" እንዳልሆኑ ይናገር እንደ ነበረ በመግለጽ ምንም እንኳን እነዚህ ነገሮች "ደስ የሚሉ፣ የሚያምሩ" ጥሩ የሆኑ ነገሮች ቢሆኑም ለእኛ ተስፋ የሚሰጡን ነገሮች አለመሆናቸውን በማብራራት ግልጽ ያደረጉ ሲሆን በእነዚህ ነገሮች ላይ በማሰላሰል እነዚህን ድንቅ ነገሮች "ማን እንደሰራቸው ፈልጉ። እነዚህ አስተያየቶች በትክክል ከሁለት ዓመት በፊት በሊዝበን በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ግብዣ ያስታውሳሉ፣  ታላቅ ጥያቄዎችን ለመጋፈጥ” “ጉዞ” በማድረግ፣ ከራስ በላይ በመሄድ  መልሱ በክርስቶስ ላይ ነው፣ አንድን ነገር በሕይወቱ ውስጥ ታላቅ ለማድረግ፣ ራስን እና ማኅበረሰብን ለማሻሻል ፍላጎትን በማነሳሳት የበለጠ ሰው እና ወንድማማችነት እንዲኖረው ያደርጋል" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ከ7ሺ በላይ ካህናት ተሳትፈዋል
በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ከ7ሺ በላይ ካህናት ተሳትፈዋል   (@Vatican Media)

ከክርስቶስ ጋር ወዳጅነት መመሥረት

ስለዚህም ከክርስቶስ ጋር “አንድ ሆነን እንድንቆይ በጓደኙነቱ ውስጥ እንድንቆይ፣ ሁልጊዜም በጸሎት፣ በስግደት፣ በቅዱስ ቁርባን፣ ደጋግመን ምስጢረ ንስሐ በመግባት፣ በመናዘዝ፣ ለጋስ በመሆን መኖር ይኖርብናል" ያሉት ቅዱስነታቸው ለወጣቶቹ በእለቱ በሰጡት የመጨረሻ ጠቃሚ ምክረ ሐሳብ “ለመጥፋት ሳይሆን ነገር ግን ለታላቅ ነገሮች ለቅድስና እንዲመኙ" ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም፣ አሁን ወደ አገራቸው ለመመለስ ለሚዘጋጁት ወጣት ወንዶች እና ሴቶች፣ “በአዳኙ በክርስቶስ ፈለግ በመመራት በደስታ መመላለሳቸውን” እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል።

04 Aug 2025, 12:07