MAP

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ዋዜማ ላይ አርቲስቶችን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ዋዜማ ላይ አርቲስቶችን በቫቲካን ሲቀበሉ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንም እውነተኛ ደስታን እናገኛለን” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቅዳሜ ሐምሌ 26/2017 ዓ. ም. ምሽት በቶር ቬርጋታ ከሚፈጸመው የወጣቶች ኢዮቤልዩ የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት ቀደም ብሎ አርቲስቶችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለአርቲስቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ከኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ወጣቶችን እንዲያስታውሱ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቅዳሜ ምሽት በሮም ቶር ቬርጋታ ከሚፈጸም የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ዋዜማ ቀደም ብሎ ባደረጉት ንግግር፥ “ሁላችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ የምናገኛቸውን እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች መርዳት ይገባል” ሲሉ በያዝነው ሳምንት ውስጥ በልዩ ልዩ የሮም ከተማ አደባባዮች ወጣቶችን ሲያበረታቱ ለቆዩት አርቲስቶች አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው ሐምሌ 26/2017 ዓ. ም. ማለዳ ላይ የአርት ቡድንን በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቀለሜንጦስ ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ተቀብለው ባሰሙት ንግግር፥ አርቲስቶቹ “በእነዚህ ቀናት ሮም ውስጥ ለበርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን ሲያቀርቡላቸው የቆዩትን ልዩ ልዩ የጥበብ እና የሙዚቃ ዝግጅቶችን አስታውሰው፥ እንደ ሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ ተልዕኮ እና አገልግሎት ላይ መሳተፍ መቻሌ ትልቅ ክብር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከእግዚአብሔር በተሰጡ ስጦታዎች በኩል እምነትን መለማመድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከአንድ መቶ አርባ ስድስት አገራት የመጡ በቁጥር በርካታ ወጣቶች ያሳዩትን መጠነ ሰፊ ተሳትፎ በማስታወስ፥ ይህ የጋራ እምነት፣ ተነሳሽነት እና ደስታ አንድ እንደሚያደርጋቸው ጨምረው ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ አርቲስቶቹ ያቀረቧቸው ዝግጅቶች እና እያበረከቷቸው ያሉት አስተዋፅኦች በልባችን ውስጥ ይዘን ለምንኖረው ነገር ድምጽ እንደሚሰጥ አስገንዝበው፥ ይህም ከሁሉም በላይ ደስታን፣ ፍቅርን እና እምነትን ለመለማመድ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

የእግዚአብሔር ስጦታዎች ሙዚቃን፣ ውዝዋዜን እና ለሌሎች የሚያካፍሏቸውን በርካታ የጥበብ ሥራዎችን እንደሚያካትት ተናግረው በመጨረሻም፥ “ይህ በእውነት ለሁላችን እና ለመላዋ ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው” ካሉ በኋላ ለአርቲስቶቹ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን በመስጠት ሸኝተዋቸዋል።

በወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ዋዜማ ላይ አርቲስቶችን በቫቲካን ተቀብለዋል
በወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ዋዜማ ላይ አርቲስቶችን በቫቲካን ተቀብለዋል   (@Vatican Media)

 

02 Aug 2025, 16:56