MAP

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የወንድማማችነት ማኅበር የተስፋ ምልክት እንዲሆን አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የወንድማማችነት አገልግሎት ማኅበር “Knights of Columbus” መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው ማኅበሩ እጅግ ለተቸገሩት ሰዎች ለሚሰጠው አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ማኅበሩ አገልግሎቱን የሚያበረክተው የመሥራቹን የሚካኤል ማክጊቭኒ ዓላማ በመከተ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በአሜሪካ ዋሽንግተን 143ኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ለማካሄድ ለተሰበሰቡት የማኅበሩ አባላት የቪዲዮ መልዕክት ልከዋል።

ቅዱስነታቸው ጉባኤውን በአካል ሆነ ከሩቅ ለሚካፈሉት በሙሉ ሰላምታ ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ ጉባኤው በኢዮቤልዩ የተስፋ ዓመት መካሄዱ ያለውን ጠቀሜታ አስምረውበት፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን በመጥቀስ፥ “ተስፋ ወደፊት ምን እንደሚያመጣ ባናውቅም  የሚመጡትን መልካም ነገሮች መሻት እና መጠባበቅ” ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ የተስፋችን ምንጭ ነው” በማለት መል ዕክታቸውን የቀጠሉት ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እያንዳንዱ የክርስቲያን ትውልድ በቃልም ሆነ በተግባር ወንጌልን ለማወጅ የተጠራ መሆኑን በማስታወስ፥ በተለይም በችግር ላይ ለሚገኙት ሰዎች የተስፋ ምልክት የመሆንን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የማኅበራቸው መሥራች ፈለግን መከተል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የወንድማማችነት አገልግሎት ማኅበር “Knights of Columbus” መሥራች ብፁዕ ሚካኤል ማክጊቭኒ አብነት ጠቁመው፥ ለስደተኛ ካቶሊካዊ ምዕመናን እና ድሆች ተጨባጭ ዕርዳታ እና መንፈሳዊ ድጋፍ በመስጠት ምላሽ መስጠቱን አስታውሰው፥ ይህ የወንድማማችነት በጎ አድራጎት ተልዕኮ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የማኅበሩ ምክር ቤቶች ሥራ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

“የተስፋ አብሳሪዎች” የሚለውን የዘንድሮው መሪ ሃሳብ የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ መሪ ሃሳቡ ማኅበርተኞቹ በቁምስናዎቻቸው፣ በማኅበረሰባቸው እና በቤተሰባቸው ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና ለማስታወስ እንደሚያገለግል ተናግረው፥ ማኅበሩ ሰዎችን ለጸሎት፣ ለሕንጸት እና ለአገልግሎት በመሰብሰብ ላደረገው ጥረት እና እንዲሁም እርጉዝ ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ ድሆችን እና በጦርነት የተጎዱትን ጨምሮ ተጋላጭ ሰዎችን ለማገልገል ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ በተናገሩት አጭር ቃል፥ ጥረታቸውን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ለብፁዕ ሚካኤል ማክጊቪኒ አማላጅነት አደራ በመስጠት፥ ለጉባኤው መልካሙን ተመኝተው ተሳታፊዎችንም በመባረክ መል ዕክታቸውን አጠናቀዋል።

07 Aug 2025, 18:58