ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደርን መርቀው እንደሚከፍቱ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ መጭው ዓርብ ነሐሴ 30/2017 ዓ. ም. በሮም ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ በአሥር ሰዓት ላይ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው ታሪካዊ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሥፍራ የሚገኘውን የአትክልት ቦታ መረቀው ለሕዝብ ክፍት እንደሚያደርጉት ታውቋል።
ይህ መንደር አስቀድሞ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል እንዲሆን በአደራ የተሰጠ ሲሆን፥ መንደሩ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮን ከእምነት ጋር በማዛመድ ለምድሪቱ እና ተጋላጭ ለሆኑት የማኅበረሰብ ክፍሎች እንክብካቤን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ተጨባጭ ምልክት እንደሚሆን ታውቋል።
135 ሄክታር ቦታን የሚሸፍነው ይህ የአትክልት ሥፍራ፣ የመኖሪያ ቪላዎችን፣ የአርኪኦሎጂ ሥፍራዎችን እና የእርሻ መሬቶችን የሚያካትት ሲሆን፥ ፕሮጄክቱ ታሪክን ከትምህርት እና ዘላቂነት ካለው የማኅበረሰብ ሕይወት ጋር እንደሚያዋህዳቸው ታውቋል።
ማዕከሉ በመግለጫው፥ መንደሩ በቀላሉ የሚጎበኝ ሳይሆን ነገር ግን በተጨባጭ የሚኖሩበት፣ የሚጸልዩበት፣ ትምህርት የሚቀስሙበት፣ ከእግዚአብሔር፣ ከእርስ በርስ እና ከፍጥረታት ጋር ኅብረትን ለመፍጠር የሚያስችል ቦታ እንደሆነ አስታውቋል።
በፍጥረት መካከል የሚደረግ ዑደት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱን የሚጀምሩት በመንደሩ ውስጥ ለዚህ አዲስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሥፍራ ፕሮጄክት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ካበረከቱት ሠራተኞች፣ ግብረ አበሮቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ምሳሌያዊ ዑደት በማድረግ እንደሚሆን ታውቋል።
ቅዱስነታቸው በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ በሥራቸው እና በትጋታቸው ለመንደሩ ምሥረታ ተልዕኮ ሕይወትን ከሰጡ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና በጎ አድራጊዎች ጋር እንደሚገናኙ ተገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከዑደቱ ቀጥለው ጸሎትን በማቅረብ የቡራኬ ሥነ-ሥርዓቱን እንደሚመሩ የዕለቱ መርሃ-ግብር አመልክቷል።
የዜማ እና የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል
የምረቃው ሥነ-ሥርዓት በጸሎት እና በዝማሬ የሚፈጸም ሲሆን፥ እውቁ ጣሊያናዊ የዜማ ደራሲ አንድሬያ ቦቼሊ ከልጁ ማቴዎ ጋር በመሆን ከቅዱስነታቸው የቡራኬ ሥነ-ሥርዓት ቀደም ብሎ የምስጋና ዜማን እንደሚያቀርብ የገለጸው መግለጫው፣ ታሪካዊ በተባለው በዚህ በዓል ላይ ከፍተኛ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈቶች ተወካዮች፣ መሪዎች እና ተባባሪዎቻቸው የሚገኙ መሆኑን አስታውቋል።