የር. ሊ. ጳ. ሊዮ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ርዕሥ “ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን” የሚል መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2026 ዓ. ም. ለሚከበረው የዓለም የሰላም ቀን የመረጡትን ጭብጥ ማክሰኞ ነሐሴ 20/2017 ዓ. ም. ይፋ ያደረገው በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሆኑ ታውቋል።
“ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን! ከጦር መሣሪያ ትጥቅ ነጻ የሆነ ዓለም” የሚለው መሪ ቃል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ዓመታዊ በዓል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር 1 ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን መመረጡ ታውቋል።
የመሪ ቃሉ ጭብጥ የሰው ልጅ የዓመፅ እና የጦርነት አመክንዮን በመቃወም በፍቅር እና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ ሰላም እንዲቀበል የሚጋብዝ መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ ሆነው በተመረጡበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 8 ቀን 2025 ዓ. ም. ምሽት እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰላም በዓለማችን እንዲሰፍን ሲማጸኑ መቆየቸው ሲታወስ፥ ይህም ከጦር መሣሪያ ትጥቅ ነጻ የሆነ ሰላምን እንደሚፈልጉ ለመግለጽ እንደሆነ ታውቋል።
“ይህ ሰላም ከጦር መሣሪያ ትጥቅ ነጻ የሆነ ማለትም በፍርሃት እና በዛቻ ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም” ያለው መግለጫው፥ የመሣሪያ ትጥቅን ማስፈታት፣ ግጭቶችን ማስቆም የሚችል፣ ልብን የሚከፈት፣ የጋራ መተማመንን፣ መተሳሰብን እና ተስፋን መፍጠር የሚችል መሆን አለበት” ሲል መግለጫው አክሏል።
“የሰላም ጥሪ ማቅረብ ብቻውን በቂ አይደለም” ያለው መግለጫው፥ የሚታይም ሆነ በእጅ አዙር የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በሙሉ የማይቀበል የአኗኗር ዘይቤን ልንይዝ እንደሚገባ አሳስቧል።
በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መግለጫ፥ ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ቁርኝታችን ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለን ሚና ምንም ይሁን ምን ሁሉም የሰው ልጅ ሰላምን እንዲፈልግ ያቀረበው ሁለንተናዊ ጥሪ እንደሆነ አመላክቷል።
“ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ዮሐ 20፡19) የሚለው “ከሞት የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምታ፥ ለሁሉም የሰው ልጅ፥ ለአማኞች፣ አማኝ ላልሆኑ፣ ለፖለቲካ መሪዎች እና ዜጎች በሙሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲገነቡ፣ ሰብዓዊ እና ሰላማዊ የወደፊት ሕይወት ለመገንባት በጋራ እንዲሠሩ የቀረበ ግብዣ ነው” ሲል መግለጫው መልዕክቱን ደምድሟል።
የር. ሊ. ጳ. ሊዮ የመጀመሪያዎቹ ንግግሮችን የያዘ አዲስ መጽሐፍ
በተናጠል የቫቲካን አሳታሚ ድርጅት (LEV) የመጀመሪያዎቹን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ ይፋዊ ንግግሮች የያዘ አዲስ መጽሐፍ ያሳተመ ሲሆን፥ “ሰላም ይሁን! በሚል ርዕሥ ለቤተ ክርስቲያን እና ለመላው ዓለም እንዲሆን በማለት በእንግሊዝኛ፣ በጣሊያንኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች የታተመው አዲሱ መጽሐፍ ከረቡዕ ነሐሴ 21/2017 ዓ. ም. ጀምሮ ገበያ ላይ እንደሚቀርብ ታውቋል።
ጋዜጣዊ መግለጫው፥ “ከጦር መሣሪያ ትጥቅ ነጻ የሆነ ዓለም” በሚል ርዕሥ በፈረንሳዊው መነኩሴ ቻርለስ-ማሪ ክርስቲያን ደ ቼርጌ አስቀድሞ የተጻፈ መሆኑን በመጥቀስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህን ርዕሥ በድጋሚ መጠቀማቸውን አስታውሷል።
በአልጄሪያ ቲቢሪን የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ገዳም አበ ምኔት የሆኑት ፈረንሳዊው መነኩሴ ቻርለስ-ማሪ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1996 ዓ. ም. ከስድስት ወንድም መነኮሳት ጋር በአልጄሪያ የሲታውያን ማኅበር ገዳም ውስጥ በሰማዕትነት ማረፋቸው ይታወሳል።
መግለጫው ብፁዕ ካርዲናል ሮበርት ፕሬቮስት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ስማቸው ሊዮ አሥራ አራተኛ የተባሉት የአልጄሪያ ሰማዕታት መታሰቢያ ዕለት በሆነው በሚያዝያ 30 ቀን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው መመረጣቸውን አስታውሷ።
መግለጫው የመጽሐፉን ይዘት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በርካታ ጉዳዮች የያዘ መሆኑን ጠቅሶ ከእነዚህም መካከል “የእግዚአብሔር ታላቅነት፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እና የሰላም ፍለጋ” የሚሉት እንደሚገኙበት ገልጿል።
መግለጫው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓሥራ አራተኛን በመጥቀስ፥ “የእርቅ ጥያቄዎቹ በፖለቲካ መስክ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሰው ልብ ላይ ያተኮሩ ናቸው” ሲል ገልጾ፥ “ሰላም እያንዳንዳችን ሌሎችን በምንመለከትበት፣ ሌሎችን በምናዳምጥበት እና ስለሌሎች የምንናገርበት መንገድ ይጀምራል” ማለታቸውን ጠቅሷል።