MAP

ር.ሊ.ጳ ሊዮ፡- ከጋዛ፣ ዩክሬን እና በጦርነት ከተመሰቃቀሉ አገሮች ወጣቶች ጋር ነን ማለታቸው ተገለጸ! ር.ሊ.ጳ ሊዮ፡- ከጋዛ፣ ዩክሬን እና በጦርነት ከተመሰቃቀሉ አገሮች ወጣቶች ጋር ነን ማለታቸው ተገለጸ!  (q)

ር.ሊ.ጳ ሊዮ፡- ከጋዛ፣ ዩክሬን እና በጦርነት ከተመሰቃቀሉ አገሮች ወጣቶች ጋር ነን ማለታቸው ተገለጸ

የዲጂታል ሚሲዮናውያን እና የካቶሊክ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች የኢዩቤሊዩ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ በሐምሌ 27/2017 ዓ.ም በሮም ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ቶር ቬርጋታ በሚባለው ሥፍራ መከናወኑ የሚታወቅ ሲሆን በአጠቃላይ ከአንድ ሚልዮን በላይ ምዕመናን በሥፍራው ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴ ታድመዋል፣ 450 በላይ ጳጳሳት ከ7ሺ በላይ ካህናት፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ተሳትፈዋል። መስዋዕተ ቅዳሴው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ተመርቷል።

የዚህ  ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ለወጣቶች ኢዮቤልዩ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ማጠቃለያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሌሎች የሰው ልጆች የተከሰቱትን “ከሁሉ የከፋ በደል” የተነሳ የሚሰቃዩ ወጣቶችን በማስታወስ በተለይ በጦርነት የተመሰቃቀለችው ጋዛ፣ ዩክሬን እና “በጦርነት ደም የፈሰሰባትን ምድር ሁሉ” በመጥቀስ በዚህ የተነሳ ከሚሰቃዩ ሰዎች ሁሉ ጎን በመሆን ጸሎት እንደምያደርጉ ተናግረዋል።

በሮማው የቶር ቬርጋታ ሜዳ የወጣቶች ኢዮቤልዩ የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ከመጠናቀቁ ጥቂት ቀደም ብሎ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በጋዛ፣ ዩክሬን ለሚሰቃዩ ወጣቶች እና በጦርነት በተመሰቃቀለው የዓለም ክፍል ለሚኖሩ ወጣቶች ያላቸውን ቅርበት እና አጋርነት ገልጿል።

"ሰላማችን እና የአለም ተስፋ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር በመተባበር በሌሎች ሰዎች ምክንያት እጅግ የከፋ ስቃይ ለሚደርስባቸው ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለእነርሱ ቅርብ ነን፣ ከጋዛ ወጣቶች ጋር ነን ። ከዩክሬን ወጣቶች ጋር ነን ፣ በጦርነት ደም ከሚፈስባቸው የምድሪቱ ክፍል ሰዎች ሁሉ ጋር ነን ። ወጣት ወንድሞቼ እና እህቶቼ ፣ እናንተ የተለየ ዓለም ለምፍጠር የሚቻልበት ምልክት ናችሁ ፣ ወንድማማችነት ፣ ግጭት እና ወዳጅነት ከሌላው ዓለም ጋር አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

ለማሪያ እና ፓስካሌ የቀረበ የሐዝን መግለጫ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱም በድንገተኛ የጤና አደጋ ምክንያት በሮም ቆይታቸው በሞቱት ስፔናዊ እና ግብፃዊት ማሪያ እና ፓስካሌ የተባሉ ሁለት ወጣት ምዕመናን ሞት የተሰማቸውን ሐዘንና ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

እግዚአብሔርን እናመሰግናለን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንን የተናገሩት የመልአከ እግዚአብሕእር ጸሎት ከመምራታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ምዕመናን የመጨረሻ ሰላምታ ሲያቀርቡ ነበር ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት።  

ለእነዚህ የኢዮቤልዩ ቀናት ስጦታ ለእግዚአብሔር ታላቅ ምስጋናቸውን እንዲገልጹ ሁሉንም ሰው ጋብዘዋል፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለመላው ዓለም የእግዚአብሔር ጸጋ በሁሉም ወጣቶች ተሳትፎ የተንፀባረቀ መሆኑን ገልፀው ከልባቸው አመስግነዋል። ከወጣቶቹ ጋር አብረው ለተገኙት በሺዎች የሚቆጠሩ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ እና የሐዋርያዊ እንክብካቤ የምያደርጉ አባቶች እና እናቶች፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያመሰገኑ ሲሆን እንዲሁም በዝግጅቱ ላይ ጸሎታቸውን ላቀረቡና መንፈሳዊ ተሳትፎ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

እ.አ.አ 2027 ዓ.ም የዓለም ወጣቶች ቀን በሴኡል፣ ኮሪያ

በመጨረሻም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሮም ይህን የኢዮቤልዩ “የተስፋ ጉዞ” ተከትሎ፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ እ.አ.አ ከነሐሴ 3 እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2027 ዓ.ም በሴኡል፣ ኮሪያ የዓለም ወጣቶች ቀንን ለማክበር ከእነሱ ጋር በሚገናኙበት ጊዜ ቀጣዩ መዳረሻ የእስያ አህጉር እንደሚሆን አስታውሰዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በልባችን ውስጥ የሚኖረው ተስፋ በክፉ እና በሞት ላይ የተነሣውን ክርስቶስን ድል እንድናበስር ጥንካሬን ይስጠን ብለዋል። እናም ይህ እውነታ ነው ለወጣት መንፈሳዊ ነጋዲያን ተስፋ እና ድፍረትን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮች እንዲሆኑ አሳስባለሁ፣ በቀጣይም በሴኡል በሚደረገው ስብሰባ ላይ አብረን እናልም እና ተስፋ እናድርግ በማለት እራሳችንን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናት እንድትጠብቀን በአደራ እንስጥ ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

 

04 Aug 2025, 13:26