MAP

የሄሊኮፕተር አደጋ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች በአክራ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ የሄሊኮፕተር አደጋ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች በአክራ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ  (ANSA)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሄሊኮፕተር አደጋ ሰለባ ለሆኑት ጋናዊያን የሐዘን መግለጫ ልከዋል።

በሐምሌ 30/2017 ዓ.ም በወታደራዊ ሄሊኮፕተር አደጋ ለሞቱት ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ሲቪሎች ሞት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የተሰማቸውን ሐዘን ለጋና የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት በተላከው የቴሌግራም መልእክት ቅዱስነታቸው ሐዘናቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ረቡዕ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ለሞቱት ሚኒስትሮች፣ የመንግስት ባለስልጣናት እና የበረራ ሰራተኞች ሞት የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹ ሲሆን የሀዘን መግለጫው የቫቲካን ዋና ጸኃፊ በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በተፈረመ የቴሌግራም መልእክት ለሱያኒ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ማቲው ኬ. ጊያምፊ እንዲሁም የጋና ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት በላኩት የሐዘን መግለጫ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

የቅድስት መንበር ኅትመት ክፍል ሐሙስ ነሐሴ 1/2017 ዓ.ም ምሽት ላይ ባወጣው የቴሌግራም መልእክት፣ “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በወታደራዊ ሄሊኮፕተር አደጋ ለሞቱት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ለሞቱት ሁሉ ሀዘናቸውን ገልፀው የሟቾችን ነፍስ ለልዑል እግዚአብሔር ምሕረት አደራ እየሰጡ፣ በደረሰባቸው ጉዳት ለሚሠቃዩት በተለይም ለቤተሰቦቻቸው፣ ቅዱስ አባታችን በጸሎት አብረዋቸው እንደሚሆኑ አስታውቀዋል" ሲል ገልጿል።

ሄሊኮፕተሩ ሶስት ሰራተኞችን እና አምስት ተሳፋሪዎችን አሳፍሮ የተከሰከሰው በማዕከላዊ አሻንቲ ክልል በደን የተሸፈነ አካባቢ ነበር። የጋና መከላከያ ሚኒስትር ኤድዋርድ ኦማኔ ቦአማህ፣ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሩ ኢብራሂም ሙርታላ መሐመድ እና አብረዋቸው የሄዱት ስድስት የአውሮፕላኑ ሰራተኞች እና ሌሎች ተሳፋሪዎች ነበሩ። ሕገ-ወጥ ማዕድን ማውጣትን ከማስቆም ጋር በተያያዘ ወደ ኦቡአሲ ከተማ እየተጓዙ ነበር። በሕይወት የተረፉ ሰዎች አልነበሩም።

ፊደስ በመባል የሚታወቀው የሚስዮናውያን የዜና አገልግሎት ኤጄንሲ  ጳጳስ ጂያምፊ ለአደጋው የሰጡትን ምላሽ ዘግቧል፣ ዜናው ለሁሉም አስደንጋጭ ነበር ብሏል። የጋና ጳጳሳት ጉባኤ ለፕሬዚዳንት፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ለፓርላማው እና ለሀገሪቱ ሕዝብ ሐዘናቸውን የገለፁ ሲሆን፥ “ሁሉም ጋናውያን እንዲጸልዩላቸው እንጠይቃለን” በማለት “እንዲህ ያሉ ድንቅ አእምሮዎችን በአንድ ጊዜ በማጣታቸው መደናገጣቸውን" ገልጿል። ጳጳሳቱ "ተጎጂዎቹ የተረጋገጡ ቁርጠኝነት ያላቸው፣ የመንግሥት አገልጋዮች፣ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃን እና የጋና ጦር ሃይሎች ለሪፐብሊኩ፣ ለተቋማቱ እና ለዚች ሀገር ህዝብ ህይወታቸውን የሰጡ ጀግኖች መኮንኖች መሆናቸውን" አፅንዖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን በድንገተኛ ሁኔታ እና ያለጊዜው ማለፋቸው ለቤተሰቦቻቸው እና ለጓደኞቻቸው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ትልቅ ኪሳራ ነው ሲሉ ባወጡት የሐዘን መግለጫ አክለው ገልጸዋል።

የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ የሶስት ቀናት ብሄራዊ ሀዘን አውጀዋል።

08 Aug 2025, 10:29