ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በየመን በደረሰ የጀልባ አደጋ በሞቱት ስደተኞች የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በየመን የባሕር ዳርቻ በደረሰ የጀልባ መገልበጥ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደ ነበሩ በሚነገርለት አደጋ በሞቱት ስደተኞች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለጹ ሲሆን፥ በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የተፈረመው የቅዱስነታቸው የቴሌግራም መልዕክት በየመን በሚገኘው የአረብ ባሕረ ሰላጤ አገራት ሐዋርያዊ እንደራሴ በሆኑት በሊቀ ጳጳስ አቡነ ዛኪያ ኤል ካሲስ በኩል ለአገሪቱ ባልሥልጣናት ተልኳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመልዕክታቸው ላይ እንደገለጹት፥ “በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ የበርካታ ስደተኞችን ነፍስ ልዑል እግዚአብሔር በምሕረት እንዲቀበል” እንዲሁም በሕይወት ለተረፉት፣ ለድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች እና በአደጋው የተጎዱት በሙሉ መለኮታዊ ጥንካሬን፣ መጽናናትን እና ተስፋን እንዲያገኙ” በማለት በጸሎታቸው አስታውሰዋል።
ሞትን የሚያስከት የጉዞ መስመር
አደጋው የተከሰተበት አካባቢ ከረጅም ጊዜ ወዲህ “ሞትን የሚያስከት መንገድ” ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ሲሆን፥ በዓለም ውስጥ ካሉት እጅግ አደገኛ ከሚባሉ የስደት መስመሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (አይኦኤም) አስታውቆ፥ የኤደን ባሕረ ሰላጤ ወደ ሳውዲ አረቢያ እና ወደ ሌሎች ሃብታም የባሕረ ሰላጤ አገራት መንግሥታት የሚያመሩበት የሕገወጥ ጀልባዎች ቁልፍ መሻገሪያ መሆኑን ድርጅቱ አስረድቷል።
ይህ የጉዞ መስመር በተለይ ከሶማሊያ እና ከኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞችን መሳብ የቀጠለ ሲሆን፥ ይህም በቅርብ ጊዜ በደረሰው አደጋ የተጎዱትን እንደሚያካትት ታውቋል። ያለፈው እሑድ ነሐሴ 27/2017 ዓ. ም. የተከሰተው አደጋ በአቢያን ግዛት የባሕር ዳርቻ ላይ ባለው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ አደጋ ብዙዎችን ለሞት እና ለመጥፋት መዳረጉ ታውቋል።
በአረብ ባሕረ ሰላጤ በምትገኝ እጅግ ድሃ አገር የመን ውስጥ ከአሥር ዓመታት በላይ የዘለቀው የትጥቅ ጦርነት አገሪቱን እያወደመ ሲሆን፥ ስደተኞች ይህችን አገር መተላለፊያቸው ሲያደርጓት አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ታውቋል።
ተጎጂዎቹ ከኢትዮጵያ የመጡ ናቸው
በቅርቡ በተፈጠረው በዚህ አደጋ የተሳተፉት ስደተኞች ከኢትዮጵያ ወደ የመን ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ይጓዙ የነበሩ ሲሆን፥ እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (አይኦኤም) ዘገባ ከሆነ 157 ሰዎች በጀልባው እንደተሳፈሩ ታምኗል። በዘገባው መሠረት እስካሁን ድረስ 76 ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፥ በሕይወት የተረፉ 32 እና በደርዘን የሚቆጠሩ የደረሱበት የማይታወቅ እና ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል የማይታወቅ መሆኑ ተነግሯል።
በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቃዊውን መስመር ለመጓዝ እንደሚሞክሩ የገለጸው ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት፥ ይህ በአሳዛኝ ሁኔታ መደበኛ ባልሆነ ስደት ብቻ ሳይሆን በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርም እንደሚታወቅ ገልጿል። የመን ውስጥ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በጉዞው ወቅት የሚደርስባቸው እንግልት እና የሚፈጸምባቸው ብዝበዛ ሰለባ እንደሚሆኑ ድርጅቱ በዘገባው አስታውቋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በጅቡቲ እና በየመን መካከል ባለው የቀይ ባሕር መስመር በትንሹ 558 ሰዎች መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (አይኦኤም) በዘገባው አስታውቋል።