MAP

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የኢየሩሳሌም ፓትርያርኮች በጋዛ ሰላም እንዲሰፍን ያቀረቡትን ጥሪ ተቀላቅለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የኢየሩሳሌም ፓትርያርኮች በጋዛ ሰላም እንዲሰፍን ያቀረቡትን ጥሪ ተቀላቅለዋል።  (@Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የኢየሩሳሌም ፓትርያርኮች በጋዛ ሰላም እንዲሰፍን ያቀረቡትን ጥሪ ተቀላቅለዋል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የላቲን እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርኮች በጋዛ ያለው ጦርነት እንዲቆም እና ሰብአዊ ርዳታ በነፃነት ወደ አከባቢው እንዲደርስ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀላቅለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በእየሩሳሌም ያሉት የላቲን እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርኮች በጋዛ ሰላም እንዲሰፍን የጋራ የሰላም ጥሪ ማክሰኞ ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም ያቀረቡ ሲሆን “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ እና በግዳጅ የሚፈጸመው መፈናቀል በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ረቡዕ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የፓትርያርኮቹን የሰላም የተማጽኖ ድምጽ ሰምተው ባለፈው አርብ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም የተደረገውን የጸሎት እና የጾም ቀን አስታውሰዋል።

"ዛሬ ለሚመለከታቸው አካላት እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ሽብርን፣ ውድመትን እና ሞትን ያስከተለውን በቅድስት ሀገር ያለው ግጭት እንዲቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ።

የሰብአዊ ርዳታ ወደ ጋዛ በሰላም እንዲገባ እና ለሲቪሎች ጥበቃ እንዲደረግም ጠይቀዋል።

አክለውም “ሁሉም ታጋቾች እንዲፈቱ፣ ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ በአስተማማኝ ሁኔታ የመግባት ሁኔታ እንዲመቻች፣ እና የሰብአዊ መብት ሕጎች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ ጥርዬን አቀርባለሁ—በተለይ ሲቪሎችን የመጠበቅ ግዴታ እና ከጋራ ቅጣት የሚያግዱትን ክልከላዎች፣ ያለ ልዩነት የሚደርገው የኃይል አጠቃቀም እና የዜጎች መፈናቀል” እንዲቆም ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በመማጸን የሰላም ጥሪያቸውን አጠናቀዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “የሰላም ንግሥት ፣ የመጽናናት እና የተስፋ ምንጭ የሆነችውን ማርያምን እንለምን” ብለዋል። " ምልጃዋ ዕርቅን እና ሰላምን በዚያች ምድር ለሁላችንም ውድ የሆነውን የሰላም ስጦታ እንዲያስገኝ እማጸናለሁ" ብለዋል።

የጋራ የሰላም ጥሪ

የእየሩሳሌም ፓትርያርኮች ባቀረቡት አቤቱታ የዓመፅ አዙሪት አብቅቶ የጋራ ተጠቃሚነትን ማስቀደም ይኖርብናል ብለዋል።

"በክልሎች እና በሰዎች ህይወት ውስጥ በቂ ውድመት ደርሷል" ብለዋል። "ሲቪሎችን እስረኞች እና ታጋቾች በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው ምንም ምክንያት የለም። በሁሉም አቅጣጫ ለረጅም ጊዜ በትዕግሥት የቆዩ ቤተሰቦችን የመፈወስ ጊዜው አሁን ነው" ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች ልቦች እንዲለወጡ ጸሎት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን በጸሎታቸውም “እኛ በፍትህ እና በህይወት ጎዳና፣ ለጋዛ እና ለመላው ቅድስት ምድር" መጸለያችንን እንቀጥላለን ማለታቸው ተገልጿ ።

ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ፣ የላቲን ፓትርያርክ እና ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ በጋዛ ከተማ በቅዱስ ቤተሰብ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጣውን የእስራኤል ጥቃት ተከትሎ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ በጋዛ የሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የሃይማኖት አባቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ የካቶሊክ እና የቅዱስ ፖርፊሪየስ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እ.ኤ.አ ከጥቅምት 7/2023 ዓ.ም የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን በአብያተ ክርስቲያናቱ ውስጥ መጠለላቸውን አስታውሰዋል።

"በማህበረሰባችን ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ሕዝብ ላይ መሬት ላይ ምን እየተከናወነ እንደ ሆነ በትክክል አናውቅም" ሲሉ የሃይማኖት አባቶች የተናገሩ ሲሆን "ቀደም ሲል የተናገርነውን ብቻ ነው የምንደግመው፡ የወደፊት ጊዜ በፍልስጤማውያን አፈና፣ ፍልስጤማውያን መፈናቀል ወይም በቀል ላይ የተመሰረተ ሊሆን አይችልም" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

 

27 Aug 2025, 13:11