ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የአርሜኒያ-አዘርባይጃን የሰላም ስምምነት አወድሰዋል!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ጦርነት “ግጭቶችን የመፍታት ዘዴ” እንደ ሆነ አድርጎ ማቅረብ ውድቅ መደረግ አለበት በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የተናገሩ ሲሆን ይህ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለመሪዎቹ ያቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ ነው። ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ለሰላም በትጋት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፣ ለዚህ ዓላማ ምእመናን መጸለይን እንዳያቆሙ አሳስበዋል ።
“ሁላችንም ጦርነቶች እንዲያበቃ መጸለያችንን እንቀጥል” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ። በሄሮሺማ እና ናጋሳኪ የቦምብ ጥቃት የተፈፀመበት 80ኛ አመት ጦርነትን በፅኑ አለመቀበል፣ ለግጭት መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አለም አቀፋዊ መነቃቃትን ቀስቅሷል ብለዋል። "በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ውሳኔያቸው በሰዎች ህይወት ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ መዘንጋት የለባቸውም" ብለዋል። በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ወይም ዓለም አቀፋዊ የሰላም ናፍቆትን ችላ ማለት የለባቸውም ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
አርሜኒያ እና አዘርባጃን ፡ የሰላም መንገድ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠል በነሐሴ 2/2017 ዓ.ም በአርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን እና በአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ የተፈረመውን ስምምነት የተስፋ ምልክት አድርገው የቆጠሩት ቅዱስነታቸው የጋራ መግለጫቸው ጉልህ የሆነ ወደፊት የሚሄድ እና “በደቡብ ካውካሰስ የተረጋጋ እና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
ለሄይቲ ሐዘን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱም ትኩረታቸውን በሄይቲ እየተካሄደ ባለው ቀውስ ላይ “በተስፋ መቁረጥ ስሜት እየተዋጡ” በሕዝብ ላይ እየደረሰ ባለው ስቃይ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገለጹ። በአገሪቱ የተንሰራፋውን “ሁሉንም ዓይነት ጥቃት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የግዳጅ መፈናቀልና አፈና” አውግዟል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "ሁሉም ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ታጋቾቹን በአስቸኳይ እንዲፈቱ ልባዊ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል። በተጨማሪም "የሄይቲ ህዝቦች በሰላም እንዲኖሩ የሚያስችል" ማህበራዊ እና ተቋማዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጨባጭ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።