ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሕይወት ጎዳና ማንም ብቻውን መጓዝ አይችልም ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በሜጁጎሪ በመካሄድ ላይ በሚገኘው 36ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለተገኙት በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣት ነጋዲያን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወጣቶች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አርአያነት እንዲከተሉ አሳስበዋል።
በቦስኒያ ሄርዞጎቪና ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በሚገኝበት በሜጁጎሪ ከሐምሌ 28 እስከ ነሐሴ 2/2017 ዓ. ም. ድረስ በመከበር ላይ በሚገኘው የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከመዝ. 122:1 የተወሰደውን እና “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” የሚለውን የዘንድሮው ፌስቲቫል መሪ ጥቅስ መሠረት በማድረግ መል ዕክት አስተላልፈዋል።
ይህ ጥቅስ ፍቅሩ ወደሚጠብቀ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የምናደርገውን ጉዞ እና በእውነት በእርሱ ቤት መሆናችን እንዲሰማን የሚያደርገንን የጉዞ ስሜት የሚቀሰቅስ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ኢየሱስ እውነተኛው መንገድ ነው
“መንገዳችንን ሳንሳሳት እንዴት ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደርሳለን?” በማለት የጠየቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ. 14፡6 ላይ “እኔ መንገድ ነኝ” ያለውን የራሱን ቃል ጠቅሰዋል።
“በመንገዳችን ላይ አብሮን የሚጓዝ፣ የሚመራን እና የሚያበረታን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “የእርሱ መንፈስ ዓይኖቻችንን እንደሚከፍት እና በራሳችን ልንረዳው የማንችለውን እንድንመለከት ያግዘናል” ብለዋል።
“በሕይወት ጎዳና ላይ ማንም ብቻውን አይጓዝም” በማለት አጽንዖት ሰጥተው፥ መንገዳችን ዘወትር ከሌሎች ሰዎች መንገድ ጋር የተገናኘ፣ የተፈጠርነውም እርስ በርስ ለመገናኘት፣ አብሮ ለመጓዝ እና የጋራ ግባችንን ለማግኘት ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቅዱስ አጎስጢኖስን አስተንትኖ በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመድረስ የምናደርገው ጉዞ የሩቅ ጊዜ ግብ ሳይሆን ነገር ግን እንደ ነጋዲያን “ኑ አብረን እንጓዝ!” በመባባል የሚገኘውን ደስታ በኅብረት የምንካፈለው እንደሆነ አስረድተዋል።
“መንፈሳዊ ነጋዲያኑ ይህን ሲያደርጉ እርስ በርሳቸው እንደ እሳት በመቀጣጠል አንድ ነበልባል እንደሚሆኑ እና ያ በውስጣቸው ያለው አንዱ ነበልባል ከፊት ለፊታቸው ያለውን መንገድ የያበራ ይሆናል” ብለዋል።
“ብቻውን የሚጓዝ ማንም የለም” በማለት ደጋግመው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “እርስ በርሳችን በመበረታታት እና በመቀጣጠል የምናወጣው የልባችን ነበልባል አንድ ላይ በመሆን ለጋራ ጉዞአችን ብርሃን የሚሆን ታላቅ እሳት ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋል።
“የተወደዳችሁ መንፈሳዊ ወጣት ነጋዲያን እናንተም ብትሆኑ ብቻችሁን አይደላችሁም” ብለው፥ የእግዚአብሔር መንገድ በኅብረት የምንጓዝበት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኖረ የእምነት ውበት ነው” በማለት አስረድተዋል።
በእመቤታችን ድንግል ማርያም አምሳል
ዕለት በዕለት በምናደርጋቸው ግንኙነቶች እና ወደ እግዚአብሔር ቤት በምናደርገው የኅብረት ጉዞ አብረን መሆን እንችላለን” ብለዋል።
ነገር ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው የ “ግሎባላይዜሽን” ዘመን፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተቀረጸ የመጣውን ዓለም በማስታወስ ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ከእግዚአብሔር ጋር፣ ከጓደኞቻችን ጋር እና ከቤተሰቦቻችን ጋር የምናደርገውን እውነተኛ ግንኝነት ሊተካ የሚችል ምንም ዓይነት ስልተ ቀመር፣ ዕይታ እና ግንኙነት የለም” ሲሉ አሳስበው፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥
እመቤታችን ማርያም የአጎቷን ልጅ ኤልዛቤትን ልትጎበኛት ስትሄድ አስቸጋሪ መንገድ እንደተጓዘች፥ ቀላል ጉዞ ባይሆንም ነገር ግን ባገኘቻት ጊዜ ደስታን እንዳጎናጸፋት፣ መጥምቁ ዮሐንስ በድንግል ማርያም ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕያውነት ባየ ጊዜ በእናቱ ማኅፀን ውስጥ እንደዘለለ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወጣቶች እንደዚሁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምሳሌ በመከተል ትክክለኛውን ግንኙነትን እንዲፈልጉ በማሳሰብ፥ “አብራችሁ ደስ ይበላችሁ! ከሚያለቅሱም ጋር ለማልቀስ አትፍሩ” በማለት አበረታተዋቸዋል።
የእምነት እና የፍቅር ቋንቋ
የባሕል እና የቋንቋ ልዩነት በሚታይበት ዓለም ውስጥ ወጣቶች ድፍረት እንዲኖራቸው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ማንኛውንም ዓይነት እንቅፋት የሚያሸንፍ እና በእግዚአብሔር ፍቅር የታገዘ የእምነት ቋንቋ አለ” ብለዋል።
በሜጁጎሪ ለ36ኛ ጊዜ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ የተገኙት ወጣቶች በሙሉ የእግዚአብሔር አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን አባላት መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ወጣቶቹ እርስ በርስ እንዲገናኙ፣ እንዲተዋወቁ፣ እንዲደጋገፉ፣ ያላቸውን እንዲጋሩ እና አብረው እንዲጓዙ ጋብዘው፥ “ወደ እግዚአብሔር ቤት የምንደርሰው አንዱ ሌላውን በማነሳሳት ብቻ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።