ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለቫቲካን ሠራተኞች አዳዲስ መብቶችን የሚያስከብር ሠነድ አጸደቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቫቲካን ሠራተኞች በወሊድ ወቅት የሚከፈልባቸው አምስት ቀናት፣ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኛ ልጆች ወላጆች በየወሩ የሚከፈልባቸው ሦስት ቀናት የተፈቀደላቸው መሆኑን ሰኞ ነሐሴ 5/2017 ዓ. ም. ታትሞ የወጣው ደንብ አስታውቋል። እነዚህ ደንቦች በቫቲካን የሠራተኛ መብቶች ውስጥ ከተካተቱት አዳዲስ ደንቦች ውስጥ ሁለቱ ሲሆኑ፥ ደንቦቹ የቫቲካን ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች ድኅንነት እና መብት የሚያሰፉ ናቸው ተብሏል።
በቫቲካን የኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት አስተዳዳሪ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ሌዶ ከተፈረመ በኋላ ሐምሌ 21/2017 ዓ. ም. ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዘንድ ቀርቦ ተቀባይነትን አግኝቷል።
ሠነዱን ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያቀረቡት የቫቲካን የኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት አስተዳዳሪ ሚስተር ማክሲሚኖ ካባሌሮ፥ በቅድስት መንበር እና በጠቅላይ አስተዳደር ውስጥ ከሚሠሩት የልዩ ልዩ መምሪያዎች ተወካዮች እና ሠራተኞቻቸው ጋር እንደሆነ ታውቋል።
በሠነዱ ውስጥ ከተካተቱት አዳዲስ ደንቦች መካከል ለቤተሰብ የሚሰጡ አበሎችን እና ጥቅማጥቅሞችን በማስመልከት የተቀመጡ የተወሰኑ አንቀጾችን ያሻሻለ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የወላጆችን የፍቃድ ቀናትን የሚመለከት እንደሆነ ታውቋል።
ሠነዱ ሠራተኛው በወሊድ ወቅት የሚከፈልባቸው አምስት ቀናትን የማግኘት መብት ያጸደቀ ሲሆን፥ እነዚህ አምስቱ የዕረፍት ቀናት እንደ ሥራ ቀናት ተቆጥረው ከሰላሳ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በሰዓታት ሳይሆን ቀናቱ መቆጠር ከተጀመሩበት ጀምሮ ሙሉ ቀንናትን በተከታታይ የመውሰድ መብትን ያረጋግጣል። ለአምስት ቀናት የሚሰጡ የዕረፍት ጊዜያት ከሠራተኛው የአገልግሎት ርዝማኔ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ተመልክቶ ሙሉ ክፍያን የማግኘት መብትን ያረጋግጣል።
የአካል ጉዳተኛ ልጆች ቤተሰቦች
የአካል ጉዳተኛ ልጆች ቤተሰቦች በሐኪም የተረጋገጠ የአካል ጉዳት ክብደት ማረጋገጫ የሚያቀርቡ ከሆነ በየወሩ ሦስት የሚከፈልባቸው ቀናት የሚፈቀድላቸው ሲሆን፥ ይህ ተግባራዊ የሚሆነው አካል ጉዳተኛ ሕጻኑ በልዩ የሕክምና ተቋም ውስጥ ሙሉ ዕርዳታን የማያገኝ ከሆነ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል።
ደንቡ የቫቲካን ሠራተኞች አካል ጉዳተኛ የቤተሰብ አባልን ለመንከባከብ በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማስቻል የተዘጋጀ ቢሆንም ነገር ግን ሃላፊነት ካለው ባለስልጣን የሚፈቀዱ ቀናት ከታለሙት ተግባራት
በስተቀር ሠራተኛው የዕረፍት ቀናትን ለሌሎች ሥራዎች ማዋል እንደማይችል ያሳስባል።
ደንቡ በተጨማሪም የአካል ጉዳተኝነት ክሊኒካዊ ግምገማ እና የጉዳቱ ክብደት መጠን የሚወሰነው በከፍተኛ የቫቲካን ጠቅላይ አስተዳደር የጤና እና ንጽሕና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የሚቀርበውን የግምገማ ሪፖርት መሠረት በማድረግ የሕክምና ቦርድ በሚሰጠው ምላሽ እንደሚሆን ይገልጻል።
አንድ ሰው ከባድ የአካል ጉዳተኛ ወይም አቅመ ቢስ መሆኑ በሕክምና ቦርድ እውቅናን የሚያገኝ ከሆነ ቤተሰቡ የቤተሰብ አበል የማግኘት መብት አለው። ይህ መብት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ተግባራዊ የሚሆነው ከቫቲካን የጡረታ አበል ጋር በተያያዘ የሕክምና ቦርድ በሚሰጠው ማረጋገጫ እንደሆነ ተገልጿል።
የቤተሰብ ድጎማዎች
የቤተሰብ ድጎማዎችን በተመለከተ ደንቡ እንደሚያብራራው፥ የመብቱ ተጠቃሚ ቤተሰቦች ልጆቻቸው በሕጋዊነት የአካል ጉዳተኞች መሆናቸውን የሚያረጋግጡ፥ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው፣ ተማሪዎች ከሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ፥ ከፍተኛ ዕድሜ እስከ 20 ዓመት የደረሳቸው፥ ወይም በቅድስት መንበር እንደተደነገገው ጠቅላላ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው እስከ 26 ዓመት ዕድሜ ድረስ የሚከታተሉ እና ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠውን የምዝገባ ወረቀት እና ይህን የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ሠነድ ማቅረብ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው ይጠይቃል።