MAP

የሮማዊት ቅድስት ፍራንችስካ ማኅበር ገዳም የሮማዊት ቅድስት ፍራንችስካ ማኅበር ገዳም 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የሮማዊት ቅድስት ፍራንችስካ ምሳሌን መከተል እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሮማዊት ቅድስት ፍራንችስካ ሕይወቷን ለእግዚአብሔር ያቀረበችበትን ስድስት መቶኛ ዓመት በማስመልከት ለማኅበርተኞቿ መልዕክት አስተላልፈዋል።በመልዕክታቸው የማኅበሩ መሥራች ቅድስት ፍራንችስካ ለወንጌል አገልግሎት ያላትን ቅንዓት፣ ለመላዕክት ያላትን ክብር፣ ለቅዱሳን ያላትን ትጋት እና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ያላትን ቁርጠኝነት አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሮማዊት ቅድስት ፍራንችስካ ሕይወቷን ለአገልግሎት ያቀረበችበትን 600ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “አብነት ለመሆን የበቃች ባለ ትዳር እና እናት ቅድስት ፍራንችስካ በጊዜው በነበረው ሰብዓዊና መንፈሳዊ ድህነት የተሰቃዩትን ለማገልገል ራሷን ለእግዚአብሔር አሳልፋ መስጠቷን አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው በቅድስት ፍራንችስካ ለተቋቋመው ማኅበር ተከታዮች ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ወደ እግዚአብሔር የብርሃን እና የሰላም መንግሥት” ለመገንባት ራሳቸውን እና ፍላጎታቸውን ለእግዚአብሔር ማቅረባቸውን ገልጸው፥ አብረዋቸው በጸሎት በመተባበራቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዩጂንዮስን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ “ማኅበረሰባችን ሴቶችን ለቤተ ክርስቲያን እና ለማኅበራዊ አገልግሎት እንደሚፈልጋቸው ገልጸው፥ እንደ ቅድስት ፍራንችስካ ያሉ ሴቶች “በወንጌል ፍቅር፣ በእግዚአብሔር ቅንዓት ተቃጥለው በትህትና መንፈስ ልዑሉን ለማገልገል የሚጓጉ እና በደካማነታቸው መጠን ራሳቸውን ለኢየሱስ ክርስቶስ በማቅረብ ሐዋርያዊ ሕይወታቸውን በንጽህና ለመኖር ይጥራሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

እንደዚሁም የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ በጸጋ የሚበረታቱ እና የሚጠነክሩ፣ የዛሬውን ኅብረተሰብ ፍላጎት እና ዝንባሌ በትኩረት የሚከታተሉ፣ ምቾት እና ቅንጦት በሌለበት ሕይወት፣ በደስተኛ ምርጫ እና በለጋስ መስዋዕትነት የሚታወቅ ጥልቅ የሆነ የወንጌል ተቆርቋሪነት ያላቸው ሴቶች ዓለማችን እንደሚያስፈልገው አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ ቅድስት ፍራንችስካ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ዓለም ለማምጣት ያሳየችውን ቅንዓት የሚገልጹ ሦስት ገጽታዎችን ሲገልጹ፥ “ለመላዕክት መሪነት ያላት ትሕትና፣ ከደጋፊዎችዋ ቅዱሳን ጋር ያላት ትብብር እና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ያላትን ቁርጠኝነት ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

በሮም እምብርት ቶር ዴ ስፔኪ በተባለ ቦታ ያለው የቅድስት ፍራንችስካ ገዳም ሥራውን መቀጠሉን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ገዳሙን ለዘመናት ሲጎበኙት ለቆዩ የቅድስት ፍራንችስካ ተከታዮች ዕውቅናን በመስጠት፥ “ብዙ የተለያየ ማኅበረሰብ በሚገኝበት በዛሬው ዓለም ይህን የመሰለ የአገልግሎት ሕይወት ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲል መንፈስ ቅዱስ ተልዕኳቸውን እንደሚረዳቸው በማረጋገጥ፥ ማኅበርተኞቹ የገቡትን ቃል እንዲያድሱ በማሳሰብ፣ ከሚመለከቷት ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድነት እንዲሰማቸው ብርታትን ከተመኙላቸው በኋላ መልዕክታቸውን ከማጠቃለያቸው በፊት ሕይወታቸውን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ለቅዱሳን አማላጅነት በአደራ በመስጠት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋቸዋል።

16 Aug 2025, 14:45