MAP

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ ስድስተኛ አዳራሽ ሳምንታዊ የጠቃላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ ስድስተኛ አዳራሽ ሳምንታዊ የጠቃላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ሊዮ ክርስቲያናዊ ፍቅር መሸሽን ሳይሆን ውሳኔን ይጠይቃል ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!” በሚለው የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማድረግ መጀመራቸው ይታወቃል፣ በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ረቡዕ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም ያደረጉት የክፍል አራት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ "“ማንን ትፈልጋላችሁ?” (ዮሐ. 18፡4) በሚለው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንደሰጠ በምያመልክተው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተንተርሰው ባደርጉት አስተምህሮ ክርስቲያናዊ ፍቅር መሸሽን ሳይሆን ውሳኔን ይጠይቃል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ/ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ንባብ

"ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። “የናዝሬቱን ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስም “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመሬት ላይ ወደቁ። ዳግመኛ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔ ነኝ፤ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ከሆነ የምትፈልጉት እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ፤ ይህም “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን እንኳን አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው" (ዩሐንስ 18፡4-9)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

ዛሬ የኢየሱስን የሕማማት ጉዞ መጀመሪያ በሚያመለክተው ትዕይንት ላይ እናተኩራለን፡ በደብረ ዘይት አትክልት ሥፍራ ውስጥ በተያዘበት ቅጽበት ላይ እናስተነትናለን። ወንጌላዊው ዮሐንስ በተለመደው የአገላለጽ ጥልቀት፣ የሚሸሽ ወይም የሚሸሸግ የፈራ የሚመስለውን ኢየሱስን አላቀረበም። በአንጻሩ የታላቁ ፍቅር ብርሃን የሚገለጥበትን ሰዓት ፊት ለፊት ቀርቦ የሚናገር ነፃ ሰው ያሳየናል።

“ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው (ዩሐ 18፡4)። ኢየሱስ የሚመጣበትን ነገር ያውቃል። ሆኖም ወደ ኋላ ላለመመለስ ወሰነ። ራሱን አሳልፎ ይሰጣል። ከደካማነት የተነሳ ሳይሆን ከፍቅር የተነሳ። በፍቅር በጣም የተሞላ፣ በጣም የበሰለ፣ እምቢተኝነትን የማይፈራ። ኢየሱስን አሳደው አልያዙትም፣ ነገር ግን እራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ እርሱን እንዲወስዱት ፈቀደ።  እሱ የእስር ሰለባ ሳይሆን ስጦታ ሰጪ ነው። በዚህ ተግባሩ፣ ለሰው ልጅ የመዳን ተስፋን ያሳያል፡ አንድ ሰው በጨለማው ሰዓት ውስጥ እንኳን እስከ መጨረሻው ድረስ ለመውደድ ነፃ ሆኖ እንደሚቆይ ለማወቅ ጠቃሚ የሆነ ምልክት ያሳያል።

ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ብሎ ሲመልስ ወታደሮቹ መሬት ላይ ወደቁ። ይህ አገላለጽ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መገለጥ ውስጥ፣ “እኔ ነኝ” የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም ከሚያስታውስበት ጊዜ ጀምሮ ምስጢራዊ ምንባብ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር መገኘት የሚገለጠው የሰው ልጅ ግፍ፣ ፍርሃት፣ ብቸኝነት ሲያጋጥመው ነው። እዚያው፣ እየመጣ ባለው ጨለማ መሸነፍን ሳይፈራ እውነተኛው ብርሃን ለማብራት ዝግጁ ነው።

በእኩለ ሌሊት፣ ሁሉም ነገር የሚፈርስ በሚመስልበት ጊዜ፣ ኢየሱስ የክርስቲያን ተስፋ መሸሽ ሳይሆን ውሳኔ መሆኑን አሳይቷል። ይህ አስተሳሰብ እግዚአብሔር ከመከራ እንዲጠብቀን ከምናደርገው ያልተጠበቀ ጸሎት የመጣ ውጤት ሳይሆን፣ ይልቁንም በፍቅር ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬን ይሰጠናል፤ ለፍቅር በነጻ የሚቀርብ ሕይወት ማንም ሊነጥቀው እንደማይችል አውቀን የምንቀበለው ጸጋ ውጤት ነው።

“እኔ ነኝ፤ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ከሆነ የምትፈልጉት እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ" (ዮሐ 18፡8) በተያዘበት ቅጽበት፣ ኢየሱስ ራሱን ለማዳን አይጨነቅም፤ ጓደኞቹ እንዲፈቱ ብቻ ይመኛል። ይህ የሚያሳየው መስዋዕቱ እውነተኛ የፍቅር ተግባር መሆኑን ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲፈቱ እርሱ ግን በወታደሮቹ እንዲያዝ ራሱን አሳልፎ ሰጠ።

ኢየሱስ በየቀኑ ለዚህ አስደናቂ እና ታላቅ ሰዓት ራሱን በማዘጋጀት ኖረ። በዚህ ምክንያት ጊዜው ሲመጣ ማምለጫ መንገድ ላለመፈለግ ጥንካሬ ይኖረዋል ማለት ነው። ለፍቅር ሲል ሕይወትን ማጣት ውድቀት እንዳልሆነ፣ ይልቁንም እንደ ስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ በወደቀች ጊዜ፣ ብቻዋን እንደማትቀር፣ ነገር ግን ሞቶ ፍሬያማ የሚሆን፣ ሚስጥራዊ ፍሬያማነት እንዳለው ልቡ ያውቃል።

ኢየሱስም ወደ ሞትና ወደ መጨረሻው የሚያደርስ የሚመስለው መንገድ ሲያጋጥመው ተጨንቋል። ነገር ግን ለፍቅር የጠፋ ህይወት ብቻ በመጨረሻ እንደሚገኝ በእኩለንት አምኗል። እውነተኛ ተስፋ የሚያካትተው ይህ ነው፡ ህመምን ለማስወገድ በመሞከር ሳይሆን እጅግ በጣም ኢፍትሃዊ በሆነ መከራ ልብ ውስጥ እንኳን የአዲሱ ህይወት ዘር እንደተደበቀ በማመን ነው።

እናም እኛስ? ምን ያህል ጊዜ ህይወታችንን፣ እቅዶቻችንን፣ ደህንነታችንን እንደምንከላከል ሳናውቅ፣ ይህን በማድረግ፣ ብቻችንን እንቆያለን። የወንጌል አመክንዮ የተለየ ነው፡ የተዘራው ብቻ ይበቅላል፤ ሁሉም ነገር የጠፋ በሚመስልበት ቦታም ቢሆን መተማመንን መመለስ የሚችለው ነፃ የሚወጣው ፍቅር ብቻ ነው።

የማርቆስ ወንጌልም ኢየሱስ በተያዘ ጊዜ "ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ጣል ያደረገ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፥ በፍታውን ጥሎ ዕራቁቱን ስለሸሸ" (ማር. 14፡51-52) በማለት ስለ አንድ ወጣት ይነግረናል። እሱ እንቆቅልሽ የሆነ ምስል ነው፣ ነገር ግን ጥልቅ ስሜት ቀስቃሽ ነው። እኛም ኢየሱስን ለመከተል በምናደርገው ሙከራ በጠባቂዎች ተይዘን የወንጌልን መንገድ ለመተው በምንፈተንበት ጊዜ ያጋጥመናል፣ ምክንያቱም ፍቅር የማይቻል ጉዞ ይመስላል። እናም ገና በእርግጥ እንደ እዚያ ጥሎ እንደ ሸሸ ወጣት ሳንሆን፣ በወንጌል መጨረሻ ላይ፣ ለሴቶች ትንሣኤ የሚያበስር፣ ነጭ ልብስ የምንጎናጸፍ እንጂ ራቁታችንን አይደለንምና።

ይህ የእምነታችን ተስፋ ነው፡ ኃጢአታችን እና ማቅማማታችን እግዚአብሔር ይቅር እንዳይለን እና የእርሱ ደቀ-መዝሙር የመሆን ፍላጎታችንን እንደገና የመቀጠል ስሜት ወደ እኛ እንዲመልስልን እና ህይወታችንን ለሌሎች አሳልፈን እንድንሰጥ አያግደንም።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ እኛም ህይወታችን ለተቀበልነው በጎ ምላሽ እንዲሆን ራሳችንን ለአብ በጎ ፈቃድ አሳልፈን መስጠትን እንማር። በህይወት ውስጥ ሁሉንም ነገር በቁጥጥር ስር ማድረግ አስፈላጊ አይደለም። በየቀኑ በነፃነት መውደድን መምረጥ በቂ ነው። ይህ እውነተኛ ተስፋ ነው፡ በፈተና ጨለማ ውስጥ እንኳን የእግዚአብሔር ፍቅር እንደሚደግፈን እና የዘላለም ህይወት ፍሬን በውስጣችን እንደሚያበስል በማወቅ መኖር ይኖርብናል።

 

27 Aug 2025, 11:09