MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል በማቅረብ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል በማቅረብ ላይ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመቀበል ልባችን ውስጥ ቦታን ማዘጋጀት አለብን” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!” በሚለው የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል አቅርበዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ረቡዕ ሐምሌ 30/2017 ዓ. ም. ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ባቀረቡት አስተምህሮ፥ “የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመቀበል ልባችን ውስጥ ቦታን ማዘጋጀት አለብን” ሲሉ አሳስበዋል።

ክቡራት ክቡራን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን የዕለቱን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ያስተነተኑበትን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ እናነብላችኋለን፥

“የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ ‘የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ አሉት’። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካ ራት የምበላበት ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳ እና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ።’ (ማር. 14: 12-16)።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ! የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት ለመረዳት የምናደርገውን እና ተስፋችን ወጥነትን የሚያገኝበት የኢዮቤልዩ ዓመት ትምህርታችንን እንቀጥል። ዛሬ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት፣ ሞት እና ትንሣኤ ምስጢር ማሰላሰል እንጀምራለን። ቀላል በሚመስል ነገር ግን ውድ የሆነ የክርስትና ሕይወት ምስጢር በያዘው “መዘጋጀት” በሚለው ላይ እናሰላስላለን።

በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ምዕ. 14 ላይ፥ ‘የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ ‘የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?’ (ማር. 14:12) የሚለውን እናገኛለን። ይህ ጥያቄ ተግባራዊ እና የሚያጓጓ ነው። ደቀ መዛሙርቱ አንድ አስፈላጊ ነገር ሊፈጸም እንደሆነ ቢረዱም ነገር ግን ዝርዝሩን አያውቁትም። የኢየሱስ ክርስቶስ መልስም እንቆቅልሽ ይመስላል፥ ‘ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል’ (ማር. 14: 13)። ዝርዝሮቹ ምሳሌያዊ ናቸው፤ ማሰሮ የተሸከመ ሰው በጊዜው የሴትነት ምልክት ነው። አስቀድሞ የተዘጋጀው የላይኛው ክፍልም የማይታወቅ የመስተንግዶ ቦታ ነው። ሁሉም ነገር አስቀድሞ የተሰናዳ ይመስላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ትክክል ነው። በዚህ ክፍል ወንጌሉ እንደሚነግረን ፍቅር የአጋጣሚ ውጤት ሳይሆን በማስተዋል የሚደረግ ምርጫ ነው። ቀላል ምላሽ ሳይሆን ዝግጅትን የሚጠይቅ ውሳኔ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደርሱበትን ሕማማት የተጋፈጠው በቁጣ ወይም በተቃውሞ ሳይሆን በነፃነት እና በጥንቃቄ፣ በታማኝነት፣ ተቀባይነት ያለውን መንገድ በመከተል ነው። የሕይወት ስጦታውን የተቀበለው በማስተዋል እንጂ በድንገተኛ ስሜት በመነሳሳት እንዳልሆነ ማወቁ ነው። እኛን የሚያጽናናንም ይህ ነው።

ያ ‘አስቀድሞ የተዘጋጀው’ የላይኛው ክፍልም እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ቀድሞ እንደሚያስብልን ይነግረናል። አቀባበል ሊደረግልን እንደሚገባ ከመገንዘባችን በፊት የእርሱ ወዳጆች እንደሆንን የሚሰማንበትን ቦታ አስቀድሞ አዘጋጅቶልናል። ይህ ቦታ ልባችን ነው። ልባችን ባዶ የሚመስል ነገር ግን በእርሱ ለመታወቅ፣ ለመሞላት እና ለመንከባከብ የሚጠብቀው ‘ክፍል’ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ሊያዘጋጁት የሚገባው የፋሲካ በዓል በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ይገኛል። እርሱ ሁሉንም ነገር አስቀድሞ አስቧል፣ አዘጋጅቷል፣ ወስኗልም። ይሁን እንጂ ጓደኞቹ የድርሻቸውን እንዲወጡ ይጠይቃል። ይህ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አስፈላጊ የሆነ ነገር ያስተምረናል። ጸጋ ነጻነታችንን አያጠፋም፤ ይልቁንም ያበረታዋል ወይም ያነቃቃዋል። የእግዚአብሔር ስጦታ ኃላፊነታችንን ፍሬያማ ያደርገዋል እንጂ አያጠፋውም።

ዛሬም ቢሆን እንደበፊቱ ሁሉ የሚዘጋጅ እራት አለ። የሥርዓተ አምልኮ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከኛ በላይ ወደሆነው ምልክት ውስጥ ለመግባት ያለን ዝግጁነት ነው። ቅዱስ ቁርባን በመሠዊያው ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር እንደ መስዋዕት እና እንደ ምስጋና በማቅረብ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ማክበር እንችላለን። ይህንን ምስጋና ለማቅረብ መዘጋጀት ማለት ብዙ መሥራት ማለት አይደለም ነገር ግን ክፍሉን ነጻ ማድረግ ማለት ነው። የሚያደናቅፉ ነገሮችን ማስወገድ፣ ፍላጎቶቻችንን መቀነስ እና የማይጨበጡ ተስፋዎችን መያዝ ማቆም ማለት ነው። በእርግጥ ብዙውን ጊዜ ዝግጅትን ከተሳሳተ ሃሳብ ጋር እናምታታለን። የተሳሳቱ ሃሳቦች ትኩረታችንን ይከፋፍሉታል። መዘጋጀት ግን ወደ መልካም መንገድ ይመራናል። የተሳሳተ ሃሳብ ወይም ቅዠት ውጤትን ይፈልጋል። መዘጋጀት ግን የእርስ በርስ ግንኙነት ተፈጻሚ እንዲሆን ያስችላል። ቅዱስ ወንጌል እንደሚያስታውሰን፥ እውነተኛ ፍቅር ምላሽን ከመስጠታችን በፊት ይገለጻል። እውነተኛ ፍቅር በቅድሚያ የሚሰጥ ስጦታ ነው። በምንቀበለው ነገር ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ነገር ግን አንድ ሰው ሊሰጥ በሚፈልገው ነገር ላይ የተመሠረተ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተጨባጭ የኖረበት መንገድ ይህ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ይህንን ገና አላስተዋሉም ነበር። ከእነርሱ መካከል አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው፥ ሌላውም ደግሞ ሊክደው ሲያስብ ሳለ እርሱ ግን ለሁሉም የሚሆን የኅብረት እራት እያዘͶላቸው ነበር።

ውድ ወንድሞችና እህቶች፣ እኛም የጌታን የ ‘ፋሲካ ራት እንድናዘጋጅ’ ተጋብዘናል። በሥርዓተ አምልኮው ብቻ ሳይሆን በሕይወታችንም ጭምር ነው። እያንዳንዱ የፈቃደኝነት ምልክት፣ ምስጋናን ማቅረብ፣ ይቅርታ ማድረግ፣ በትዕግስት የሚደረግ ጥረት፥ እነዚህ በሙሉ እግዚአብሔር የሚኖርበትን ቦታ ለማዘጋጀት የሚረዱ መንገዶች ናቸው። ስለዚህ እራሳችንን እንዲህ ብለን እንጠይቅ፥ ‘ጌታን በሕይወቴ ውስጥ ለመቀበል ማዘጋጀት ያለብኝ ቦታ የቱ ነው?’ ‘መዘጋጀት’ ማለት ዛሬ ለእኔ ምን ማለት ነው? ምናልባት ሊደረግልኝ የምፈልገውን ነገር መተው ነው? ሌሎች እንዲያስተካክሉልኝ መጠበቅን ማቆም? ሃላፊነትን በቅድሚያ መውሰድ? ምናልባት ይበልጥ ማዳመጥ? በጥቂቱ ብቻ መሥራት ወይም አስቀድሞ በተዘጋጀው ነገር ላይ መተማመን እንዳለብኝ መማር?

ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በርሳችን የምንገናኝበትን ቦታን ለማዘጋጀት የቀረበልንን ግብዣ ከተቀበልን፥ ወደተዘጋጀልን ክፍል የሚመሩን ምልክቶች ማወቅ፣ ማድረግ ያለብንን የግንኙነት ዓይነቶችን እና ቃላትን፣ ሰፊ እና አስቀድሞ የተዘጋጀልን ቦታ የቱ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን። በዚህም ውስጥ እኛን የሚደግፈን እና ሁል ጊዜም የሚቀድመን የዘላለም ፍቅር ምስጢር ሳያቋርጥ እናከበራለን። እርሱ የሚገኝበትን ቦታ የምናዘጋጅ ትሑት ልጆቹ እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን። ፍቅር በሚገኝበት ቦታ ሕይወት በእውነት ማበብ ስለሚችል በዕለት ተዕለት ዝግጁነታችን ሁሉን ነገር በነጻ ልብ እንድንጋፈጥ የሚያስችለን የረጋ መተማመን በእኛ ውስጥ ሊያድግ ይገባል።”

 

06 Aug 2025, 17:01