ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እውነተኛ እምነት በቃል እና በተግባር የታገዘ ነው” ሲሉ አስገነዘቡ
ክቡራት እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ነሐሴ 18/2017 ዓ. ም. በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዛሬው ዕለት ከሉቃስ 13፡22-30 ተወስዶ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ዋና እምብርት እና ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሰው 'ጥቂቶች ብቻ ይድናሉ ወይ?' ብሎ ላቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ ውስጥ የተጠቀመበትን የ 'ጠባብ በር' ምስል እናገኛለን። ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ መልስ ላይ ‘በጠባብዋ በር በኩል ለመግባት ብዙዎች ይጋደላሉ፤ ነገር ግን አይችሉም’ ሲል ተናግረዋል (ሉቃ. 13፡24)።
ይህ ታሪክ ከሁሉ አስቀድሞ እንድናስብ ያደርገናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር የፍቅር እና የምሕረት አባት ከሆነ እና እኛን ሊቀበለን ዘወትር እጆቹን ዘርግቶ የሚጠብቀ ከሆነ ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘የመዳን በር ጠባብ ናት’ ያለው ለምንድነው?
በእርግጥ እግዚአብሔር እኛ ተስፋ እንድንቆርጥ አይፈልግም። ይልቁንም ንግግሮቹ በዋነኝነት የዳኑ የሚመስላቸው፣ ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ እና የሚያስፈልገውም ይህ ብቻ እንደሆነ የሚሰማቸውን ሰዎች ግምት ለመቃወም ነው። እነዚህ ልባቸውን ሳይቀይሩ ነገር ግን ሃይማኖታዊ ተግባራትን ማከናወን በቂ እንዳልሆነ አልተገነዘቡም። እግዚአብሔር አምልኮአችን ከሕይወታችን እንዲነጠል አይፈልግም። ለሌሎች ሰዎች ያለንን ጥልቅ ፍቅር በተጨባች የማናሳይ ከሆነ እና ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ፍትህን እስካልሰጠን ድረስ እግዚአብሔር በመስዋዕት እና በጸሎት ብቻ አይደሰትም። ስለዚህም እንዲህ ዓይነት ሰዎች አብረነው በልተናል አብረነው ጠጥተናል ብለው በመኩራራት ወደ እግዚአብሔር ቀርበው በጎዳናዎቻቸው ሲያስተምሩ፥ እግዚአብሔር ግን፥ ‘ከወዴት እንደ መጣችሁ እኔ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች ሁሉ ከእኔ ራቁ!’ ሲላቸው ይሰማል (ሉቃ. 13፡28)።
ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! በዛሬው ወንጌል ላይ የቀረበው ተግዳሮት ሊታሰብበት የሚገባ ነው። አንዳንድ ጊዜ ከእምነት ጎዳና የራቁትን ልንፈርድባቸው ብንችልም፥ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የአማኞችን ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል። እምነትን በቃላት መመስከር፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከእርሱ ጋር በመሆን ቅዱስ ቁርባንን መቀበል፣ ከእርሱ ጋር መብላት እና መጠጣት ወይም የክርስትናን አስተምህሮ ጠንቅቆ ማወቅ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ይነግረናል። እምነታችን ትክክለኛ የሚሆነው ሙሉ ሕይወታችንን ሲያቅፍ፣ ለውሳኔዎቻችን መመዘኛ ሲሆን፣ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ስንቆርጥ እና ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ በዚህ ምክንያት ለሚደርስብን አደጋ ሃላፊነት ስንወስድ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ቀላል የሆነ የስኬት ወይም የስልጣን መንገድ አልተከተለም። ይልቁንም እኛን ለማዳን ሲል በጠባብዋ የመከራ በር በኩል እስከማለፍ ድረስ ወዶናል። ኢየሱስ ክርስቶስ የእምነታችን ትክክለኛ መለኪያ ነው። እርሱ ለእኛ ያለንን ፍቅር በመግለጽ እና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ፍትህን እና ሰላምን ለማስፈን የሚያግዝ የመዳን በር ነው (ዮሐ. 10፡9)።
አስቸጋሪ እና መልካም ያልሆኑ ውሳኔዎችን የምናደርግባቸው ጊዜያት አሉ። የራስ ወዳድነት ዝንባሌዎቻችንን የምንቃወምባቸው፣ ራሳችንን ለአገልግሎት የምንሰጥባቸው እና ክፉ አመክንዮ የበላይ በሚመስልበት ጊዜ ትክክለኛውን ነገር በማድረግ መጽናት እና የመሳሰሉትን የሚያካትቱ ጊዜያት አሉ። ያንን ጊዜ አንዴ ከተሻገርን በኋላ ግን ሕይወት እንደ አዲስ የሚያብብ መሆኑን እንገነዘባለን። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ታላቅ የእግዚአብሔር ልብ እና እርሱ ባዘጋጀልን ዘላለማዊ ግብዣ ውስጥ በደስታ እንገባለን።
በቅዱስ ወንጌል ውስጥ በተጠቀሰው ‘በጠባቡ በር’ በኩል ለማለፍ ድፍረትን ለማግኘት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትረዳን እንለምን። ይህም ለእግዚአብሔር አፍቃሪ አባታችን ሰፊ እቅፍ እራሳችንን በደስታ እንድንከፍት ያግዘናልና።”