ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የሞዛምቢክ መሪዎች ሰላምን እና ደህንነትን ወደነበረበት እንዲመልሱ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሁድ ዕለት ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ማጠቃለያ ላይ የዓለምን ትኩረት በመሳብ ባሰሙት ንግግር፥ በዓመፅ እና በጦርነት የሚሰቃዩ ክልሎች ሕዝቦችን በጸሎት እና ተጨባጭ ዕርዳታን በማቅረብ ማገዝ እንደሚገባ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
የሞዛምቢክ ሕዝብን ማስታወስ እንደሚገባ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅድሚያ ሞዛምቢክ ውስጥ አክራሪዎች በሚፈጽሙት ጥቃት ለዓመታት በጸጥታ ችግር ለሚገኝ የካቦ ዴልጋዶ ሕዝብ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። በሰሜናዊው ግዛት በተፈፀሙ ጥቃቶች ምክንያት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2017 ዓ. ም. ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሰደዱ መገደዳቸው ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በንግግራቸው፥ “የአመጽ ሰለባ ለሆኑት የካቦ ዴልጋዶ ሰዎች ያለኝን ቅርበት እገልጻለሁ” ብለው፥ ምእመናን በሙሉ እነዚህን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዳይዘነጉ በማሳሰብ፥ የሞዛምቢክ መሪዎች የሚያደርጉት ጥረት ደህንነትን እና ሰላምን ወደ ነበረበት በመመለስ ስኬታማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ዩክሬንን በጸሎት ማስታወስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ በጦርነት መቅሰፍት የሚሰቃዩትን ለማስታወስ በሚል ዓላማ ዓርብ ነሐሴ 16/2017 ዓ. ም. የተደረገውን የጸሎት እና የጾም ቀንን አስታውሰው፥ ከዚህም ጋር በዩክሬን የነጻነት ቀን መታሰቢያ ላይ የቀረበውን ዓለም አቀፍ የጸሎት ተነሳሽነት ገልጸዋል። በንግግራቸው መደምደሚያም፥ “ለዩክሬን ሰላም በቀረበው ዓለም አቀፍ ጸሎት አማካይነት በጦርነት ለተሰቃየች አገራቸው እግዚአብሔር ሰላምን እንዲሰጥ ከሚልምኑ የዩክሬን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር እንተባበራለን” ሲሉ ተናግረዋል።