MAP

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ በወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ላይ ከወጣት ነጋዲያን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጡ

ከዓለም ዙሪያ የመጡ በሚሊዮን የሚገመቱ ወጣቶች በሮም የተዘጋጀውን የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት ተካፍለዋል። በዋዜማው ሥነ-ሥርዓት ላይ ወጣት ነጋዲያን ስለ ጓደኝነት፣ ስለ ሕይወት ምርጫ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስለ መገናኘት በሚሉት ርዕሦች ዙሪያ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ቅዱስነታቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቅዳሜ ሐምሌ 26/2017 ዓ. ም. ምሽት በቶር ቬርጋታ በተፈጸመው የወጣቶች ኢዮቤልዩ የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት ላይ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች የተገኙ ሲሆን፥ በዕለቱ የቀረቡትን የዝማሬ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት እና የቅዱስ ቁርባን ስግደት ሥነ-ሥርዓትቶች በጸሎት መርተዋል።

በዝግጅቱ ላይ የጥያቄ እና መልስ ክፍለ ጊዜ የነበረ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከወጣት ነጋዲያን በኩል ለቀረቡላቸው ሦስት ጥያቄዎች በስፓኒሽ፣ በጣሊያን እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከሜክሲኮ የመጣች ወጣት ዱልሴ ማርያን ሲያገኟት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከሜክሲኮ የመጣች ወጣት ዱልሴ ማርያን ሲያገኟት   (@Vatican Media)

ጓደኝነት፣ የሕይወት ምርጫዎች እና ከኢየሱስ ጋር መገናኘት

የመጀመሪያው ጥያቄ ከላቲን አሜሪካ አገር ሜክሲኮ ከመጣች የ23 ዓመቷ ዱልሴ ማርያ የቀረበላቸው ሲሆን፥ አስደሳች የሚመስል ምናባዊ የበይነ መረብ ላይ ግንኙነቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት፥ “ወደ እውነተኛ ተስፋ የሚመራንን እውነተኛ ጓደኝነት እና ፍቅር እንዴት ማግኘት እንችላለን?” የሚል እንደ ነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ ምንም እንኳን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለውይይት ልዩ ዕድል ቢሰጡም፥ እኛን በማሳመን በፍጆታ ሱስ እንድንያዝ ማድረግ እንደሚችሉ አሳስበው፥ ወዳጅነት በእውነት ዘላቂ ሊሆን የሚችለው በእግዚአብሔር ላይ ሲመሠረት ብቻ እንደ ሆነ አበክረው ገልጸዋል። ቅዱስ አጎስጢኖስን ጠቅሰው ሲናገሩ፥ “ወዳጁን የሚወድ ሰው እግዚአብሔርን በእውነት የሚወድ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥቷል።

ለቅዱስነታቸው የቀረበላቸው ሁለተኛው ጥያቄ ከጣሊያን የመጣችው የ19 ዓመቷ ወጣት ጋያ ያቀረበችው ሲሆን፥ ብዙ ወጣቶችን ደካማ አድርጎ ስለሚያስቀር እና አስፈላጊ የሕይወት ምርጫዎችን እንዳያደርጉ ስለሚከለክለው የጥርጣሬ ሁኔታን የተመለከተ እንደ ነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይህን ጥያቄ በማስመልከተ በሰጡት ምላሽ፥ እነዚህ ምርጫዎች አንድን ዕቃ የመምረጥ ጉዳይ ሳይሆን አንድን ሰው የመምረጥ ጉዳይ እንደ ሆነ አጽንዖት ሰጥተው፥ ምርጫ በምናደርግበት ወቅት ማን መሆን እንደምንፈልግ መወሰን ይኖርብናል ብለዋል።

የመጨረሻው እና ሦስተኛው ጥያቄ ከአሜሪካ ከመጣው የ20 ዓመት ወጣት ዊል ሲሆን፥ ወጣቱ በጥያቄው “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በእውነት መገናኘት የምንችለው እንዴት ነው? በፈተና እና በጥርጣሬ ውስጥ ሆነን ከእርሱ ጋር ለመገናኘታችን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?” የሚል እንደ ነበር ተደምጧል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይህን ጥያቄ በማስመልከት ለወጣት ነጋዲያን በሰጡት ምላሽ፥ “ወጣቶች በአኗኗራቸው ላይ እንዲያስቡበት፣ ፍትሕን እንዲፈልጉ፣ ድሆችን እንዲያገለድሉ እና በቅዱስ ቁርባን ውስጥ ለሚገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰግዱ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የኢዮቤልዩ መስቀል ተሸክመው ወደ በዓሉ ሥፍራ ሲደርሱ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የኢዮቤልዩ መስቀል ተሸክመው ወደ በዓሉ ሥፍራ ሲደርሱ   (@Vatican Media)

ወጣት ማርያን እና ወጣት ፓስካልን በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከወጣት ነጋዲያን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፥ በወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ቀናት ውስጥ ሕይወታቸውን ያጡትን ሁለቱ ወጣት ሴቶች፥ ከስፔን የመጣች የ20 ዓመቷ ወጣት ማርያን እና ከግብፅ የመጣች የ18 ዓመት ወጣት ፓስካልን ጠቅሰዋል።

“ለእነዚህ የተስፋ ነጋዲያን አብረን እንጸልይላቸው” በማለት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው እና ለማኅበረሰባቸው እንጸልይ” ብለው፥ “ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መንግሥቱ በሰላም እና በደስታ ይቀበላቸው” በማለት ጸሎት አድርሰዋል።

ቅዳሜ ሐምሌ 26/2017 ዓ. ም. ምሽት በቶር ቬርጋታ ለአንድ ሰዓት ያህል ቆይቶ የተጠናቀቀው የቅዱስ ቁርባን ስግደት ሥነ-ሥርዓት በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝኛ፣ በስፓኒሽ፣ በጣሊያንኛ፣ በፖርቱጋሊኛ፣ በጀርመንኛ እና በፖላንድኛ ቋንቋዎች በቀረቡ ዝማሬዎች እና ጸሎቶች የታጀበ እንደ ነበር ታውቋል።

በዋዜማው ሥነ-ሥርዓት ላይ በሚሊዮን የሚገመቱ ወጣቶች ተገኝተዋል
በዋዜማው ሥነ-ሥርዓት ላይ በሚሊዮን የሚገመቱ ወጣቶች ተገኝተዋል   (@Vatican Media)
የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ዋዜማ ሙሉ የቪዲዮ ቅንብር
04 Aug 2025, 16:58