ር.ሊ.ጳ ሊዮ የሕይወታችንን ሀብት በፍቅር እና በምሕረት ውስጥ ፈሰስ እናድርግ ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በወቅቱ ያደርጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተተሉን።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!
በዛሬው ወንጌል ኢየሱስ ሕይወታችን የሆነውን ሀብት እንዴት መጠቀም እንደሚገባን እንድናስብ ጋብዞናል (ሉቃስ 12፡32-48)። “ንብረታችሁን ሽጡ ምጽዋትንም ስጡ” (ሉቃስ 12፡33) ይላል።
እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች ለራሳችን ብቻ ጠብቀን እንዳንይዝ ይልቁንም ለሌሎች በተለይም የእኛን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በልግስና እንድንሰጥ ይመክረናል። ያለንን ቁሳዊ እቃዎች መጋራት ብቻ ሳይሆን ክህሎታችንን፣ ጊዜያችንን፣ ፍቅራችንን፣ መገኘትን እና ርህራሄን ለሌሎች አገልግሎት መስጠት ነው። ባጭሩ፣ እያንዳንዳችንን በዋጋ ሊተመን የማይችል እና የማይደገም መልካም፣ ሕያው ንብረት የሚያደርገን በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ማልማት እና ለማደግ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ መደረግ አለበት። ያለበለዚያ እነዚህ ስጦታዎች ይደርቃሉ እና ዋጋቸው ይቀንሳል፣ ወይም እንደ ሌባ የሚነጥቀው በቀላሉ የሚበላ ነገር አድርገው የሚወስዱት ይሆናሉ።
እኛ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ነን፣ የእግዚአብሔር ስጦታ ደግሞ በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። ወደ ሙላት ለመምጣት እና ራሳችንን ለመግለጽ ቦታ፣ ነፃነት እና ግንኙነቶች እንፈልጋለን። ሁሉንም የህልውናችንን ገፅታዎች የሚቀይር እና የሚያጎናጽፍ ፍቅር እንፈልጋለን። ኢየሱስ እነዚህን ቃላቶች የተናገረው ወደ እየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ ሳለ፣ ራሱን በመስቀል ላይ ለደህንነታችን በሚያቀርብበት ወቅት ያለምክንያት የተናገራቸው ቃላት አይደሉም።
የምሕረት ሥራዎች የመኖራችንን ሀብት አደራ የምንሰጥበት እጅግ አስተማማኝ እና ትርፋማ ባንክ ናቸው፤ ምክንያቱም በዚያ፣ ወንጌሉ እንደሚያስተምረን፣ “በሁለት ትናንሽ የመዳብ ሳንቲሞች” ድሃዋ መበለት እንኳ በዓለም ላይ እጅግ ባለጸጋ ትሆናለች (ማር. 12፡41-44)።
በዚህ ረገድ ቅዱስ አውግስጢኖስ እንዲህ ይላል፡- “አንድ የመዳብ ሳንቲም ሰጥተህ አንድ የብር ሳንቲም ከተቀበልክ እና አንድ የወርቅ ሳንቲም ከተቀበልክ በዕድልህ ደስ ይልሃል፤ የሰጠኸው ነገር በእርግጥ ይለወጣል፤ ወርቅ ሳይሆን ብር ሳይሆን የዘላለም ሕይወት ወደ አንተ ይመጣል” ይላል። እናም ለምን እንደሆነ ያብራራል፦ "እሱ ይለወጣል፣ ምክንያቱም አንተ ራስህ ትለወጣለህ" በማለት ተናግሯል።
በዚህ ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት ልጆቿን የምታቅፍ እናት ማሰብ እንችላለን፡ በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ በጣም ቆንጆ እና ባለጸጋ አይደለችምን? ወይም የወንድ ጓደኛ እና የሴት ጓደኛ አብረው ሲሆኑ እንደ ንጉስ እና ንግሥት እንደ ሆኑ አይሰማቸውምን? ሌሎች ብዙ ምሳሌዎችን ልናስብ እንችላለን።
ስለዚህ፣ የትም ብንሆን፣ በቤተሰብ፣ በደብራችን፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ፣ በፍቅር ለመንቀሳቀስ ማንኛውም ዕድል እንዳያመልጠን መሞከር አለብን። ይህ ኢየሱስ ከእኛ የሚጠይቀው የንቃት ዓይነት ነው፡ እርስ በእርሳችን የመተሳሰብ፣ ዝግጁ እና ተቆርቋሪ የመሆን ልማዳችንን እንድናሳድግ፣ እርሱ ከእኛ ጋር በእያንዳንዱ ጊዜ አብሮን ይጓዛል።
እህቶቼ እና ወንድሞቼ፣ ይህንን ፍላጎት እና ኃላፊነት ለማርያም አደራ እንስጥ፡ እሷ የማለዳ ኮከብ፣ ብዙ መለያየት በሚታይበት አለም የምሕረት እና የሰላም ጠባቂዎች እንድንሆን ትርዳን።