MAP

የአልባኖ ሀገረ ስብከት ካሪታስ የበጎ አድራጎት ድርጅት የአልባኖ ሀገረ ስብከት ካሪታስ የበጎ አድራጎት ድርጅት 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከአልባኖ ሀገረ ስብከት ድሃ ቤተሰቦች ጋር ማዕድ እንደሚጋሩ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ መጭው እሁድ ነሐሴ 11/2017 ዓ. ም. በሮም አቅራቢያ በሚገኝ አልባኖ ሀገረ ስብከት መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ የዕለቱ መርሃ ግብራቸው አመልክቷል። ቀጥለውም በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ ድሃ ቤተሰቦች መካከል መቶ ከሚሆኑት ጋር ምሳን እንደሚጋሩ የሚጠበቅ ሲሆን፥ የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት የሀገረ ስብከቱ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ” ዳይሬክተር እንደተናገሩት፥ ተጋባዥ ቤተሰቦች ከቅዱስነታቸው ጋር በመገናኘት ታሪኮቻቸውን እና የሕይወት ትግላቸውን ለማካፈል የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማኅበረሰቡ መካከል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች በአስተናጋጁ ተጋብዘው ወደ ፊት እንዲቀርቡ እና በገበታው ምርጥ ቦታ ላይ እንዲቀመጡ ይጋበዛሉ። እሑድ ነሐሴ 11/2017 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ውስጥ የሚሆነው ይህ ነው። ርዕሠ ሊቀ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በዕለቱ የሚቀርበውን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከመሩ በኋላ ከአልባኖ ሀገረ ስብከት የበጎ አድራጎት ሠራተኞች እና ከሀገረ ስብከቱ ድሃ ማኅበረሰብ ጋር በጳጳሳዊ መኖሪያ ግቢ የአትክልት ሥፍራ በሚዘጋጅላቸው የምሳ ግብዣ ላይ ይገኛሉ።

እሁድ ነሐሴ 11/2017 ዓ. ም. ካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ጳጳሳዊ መኖሪያ ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር በገበታ ዙሪያ ሆነው ማዕድ የሚጋሩት ድሆች ገላ መታጠቢያ እና ለበዓሉ የሚሆን ንጹህ ልብስ ከተገኘ ብለው መጠየቃቸውን የሀገረ ስብከቱ ካቶሊካዊ በጎ አድራጎት “ካሪታስ” ዳይሬክተር አሌሲዮ ሮሲ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኝ "ውዳሴ ላንተ ይሁን" የአታክልት ሥፍራ
በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኝ "ውዳሴ ላንተ ይሁን" የአታክልት ሥፍራ

እንግዶቹ አልባኖ ከተማ ውስጥ ባለው አደባባይ በኩል ወደ ጳጳሳዊ መኖሪያ ቤት እንደሚደርሱ የተናገሩት አቶ አሌሲዮ ሮሲ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከእንግዶች ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚቀመጡ ገልጸው፥ ማዕዱን በጋራ የሚካፈሉት እንግዶች አልባኖ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የ “ካሪታስ” ዕርዳታ ድርጅት የሚታገዙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በአልባኖ የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ወደ ቦታው በድጋሚ በመምጣት ከድሆች ጋርም እንዲገናኙ ምኞት እንደ ነበራቸው የተናገሩት ዳይሬክተሩ፥ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ሞንሲኞር ቪንቼንዞ ቪቫ ሃሳባቸውን በመልካምነት መቀበላቸውን ገልጸው፥ ወደ ግብዣው የሚመጡ መቶ የሚሆኑ ተረጂ እንግዶች በቶርቫያኒካ ለቤተሰቦች እና ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች በተሠራው የ “ካርዲናል ፒዛርዶ” መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ እና በ “ፍራንቼስኮ” መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ወንዶች እና በጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚኖሩ አባቶችን እንደሚያካትት አስረድተው፥ ከዚህም በተጨማሪም በአቅራቢያው በሚገኙ አንዚዮ እና ኔቱኖ ከተሞች በሚገኙ ማዕከላት ውስጥ የሚኖሩ ቢያንስ ሰላሳ ቤት የሌላቸው ሰዎች በግብዣው ላይ ለመገኘት እንደሚመጡ ተናግረዋል።

የአልባኖ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ቪንቼንዞ ቪቫ
የአልባኖ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ቪንቼንዞ ቪቫ

ሀገረ ስብከታቸው ሰፊ መሆኑን የገለጹት የ “ካሪታስ” ዳይሬክተር አቶ አሌሲዮ ሮሲ፥ የተለያዩ ዓይነት የድኅነት ሕይወት እንደሚያጋጥማቸው ገልጸው፥ እጅግ አሳሳቢ ከሆኑት መካከል አንዱ የባሕር ዳርቻ ሕይወት እንደሆነ ተናግረው፥ አንዚዮ፣ አርዲያ፣ ቶር ሳን ሎሬንሶ፣ ቶርቫያኒካ ተብለው በሚጠሩ የባሕር ዳርቻ ከተሞች ውስጥ የገላ መታጠቢያ፣ የልብስ ማጠቢያ አገልግሎት እና የአንድ ሌሊት መጠለያን የሚፈልጉ በርካታ ቤት የሌላቸው የጣሊያን እና የውጭ አገር ዘጎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

በአካባቢው በዋናነት የሚያጋጥማቸው “ደሃ ሠራተኞች” የሚባሉ ቤተሰቦች እንደሆኑ የተናገሩት የ “ካሪታስ” ዳይሬክተር አቶ አሌሲዮ ሮሲ፥ እነዚህ ቤተሰቦች በጤና አገልግሎት ክፍያ እጦት እና በሥራ ማጣት ምክንያት ኑሮአቸውን መምራት የማይችሉ ሰዎች መሆናቸውን አስረድተው፥ ብዙው ጊዜ ያለ ዕርዳታ ወሩን ማሳለፍ የማይችሉ በመሆናቸው “ካሪታስ” ካመቻቸላቸው ገበያዎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

በአልባኖ ሀገረ ስብከት የሚገኝ መመገቢያ ጣቢያ
በአልባኖ ሀገረ ስብከት የሚገኝ መመገቢያ ጣቢያ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. 3,580 ቤተሰቦችን ጨምሮ ለ 49,500 ግለሰቦች ዕርዳታ ማከፋፈላቸውን የገለጹት አቶ አሌሲዮ ሮሲ፥ በ 2024 ዓ. ም. የመጀመሪያዎቹ አሥር ወራት ለ13,000 ሰዎች ምግብ ነክ ያልሆኑ አስፈላጊ ነገሮችን ማደላቸውን እና በ “ካሪታስ” የህክምና ክሊኒኮች ለ473 ሰዎች እንክብካቤ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

እውነተኛ የቤተሰብ መንፈስ ያለበት ድባብ ለመፍጠር እንደሚፈልጉ የገለጹት አቶ አሌሲዮ ሮሲ፥ ሁሉም ሰው ስሜታዊ እና ደስተኛ እንደሆነ አስረድተው፥ ብዙዎች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን ለማሳረግ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት በአልባኖ የ “ካሪታስ” ማዕከል ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸውን ተናግረው፥ በርካታ ቤት የሌላቸው እንግዶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር ተገናኝተው የሕይወት ታሪካቸውን እና ችግሮቻቸውን ለማካፈል የጓጉ መሆናቸውን በአልባኖ ሀገረ ስብከት የሚገኝ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ” ዳይሬክተር አቶ አሌሲዮ ሮሲ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል። 

ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው የአልባኖ ሀገረ ስብከት ድሃ ቤተሰቦች
ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው የአልባኖ ሀገረ ስብከት ድሃ ቤተሰቦች

 

 

 

13 Aug 2025, 16:47