MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለቅዱስ እንድርያስ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለቅዱስ እንድርያስ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ወንጌልን መስበክ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት መመስከር መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሮም የሚገኘው የቅዱስ እንድርያስ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት አባላትን በቫቲካን ተቀብለዋል። አባላቱ ወደ ቫቲካን የመጡት የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ሲሆን ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን እና ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊን እንደ አብነት በመጥቀስ፥ “የተጠመቀ በሙሉ የሰማውን ለሌሎች ያስተላልፋል” ሲሉ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የወንጌል ትምህርት የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ተልዕኮን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጹ፥ “የእያንዳንዱ የወንጌል ትምህርት ቤት ቁልፍ ተግባር ወንጌልን መስበክ እና ሕይወት ሰጭ ከሆነው እግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት መመስከር ነው” በማለት ዓርብ ነሐሴ 23/2017 ዓ. ም. በቀሌሜንጦስ አዳራሽ ለተቀበሏቸው እና የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ቫቲካን ለመጡት በሮም የሚገኝ የቅዱስ እንድርያስ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት አባላት ተናግረዋል።

የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ አብነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከብፁዕ ካርዲናል ጄራልድ ሳይፕሪያን ላክሮክስ በካናዳ የኪቤክ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ እንድርያስ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት ዋና ጸሐፊ እና ከፕሮፌሰር ሆሴ ፕራዶ ፍሎሬስ የትምህርት ቤቱ መሥራች እና ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ “በዛሬው ዕለት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሰማዕትነት መታሰቢያ በዓል ታከብራለች” ሲሉ አስታውሰው፥ የዮሐንስ ወንጌል መቅድም፥ “ወንጌልን የሚመሰክር በሙሉ፥ ሥጋ ስለሆነው ቃል እንደሚመሰክር ገልጾታል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱስ እንድርያስ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት አባላትን በቀሌሜንጦስ አዳራሽ ሲቀበሉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱስ እንድርያስ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት አባላትን በቀሌሜንጦስ አዳራሽ ሲቀበሉ   (@Vatican Media)

ያየነውን እና የሰማነውን ማወጅ

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመሪያ መልዕክቱ ስለ ወንጌላዊነት ተልዕኮ ትርጉም እና ዓላማ ሲናገር፥ “ያየነውን እና የሰማነውን” ማለቱን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በመጀመሪያ መልዕክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ፥ ‘ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ለእናንተ ደግሞ እንሰብካለን፤ ኅብረታችን ከአብ እና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው’ የሚለውን እናነባለን” ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ከስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት ወጣት ባለትዳሮች የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ከስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት ወጣት ባለትዳሮች የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ   (@Vatican Media)

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ መሆን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የእያንዳንዱን ክርስቲያን የመጨረሻ ግብ የሚያመለክተው እና በቅዱስ አውግስጢኖስ ስብከት ውስጥ የተጻፈውን መሪ ቃል በመጥቀስ፥ የእያንዳንዱን የካቶሊክ እምነት ተከታይ የወንጌል ተልዕኮን ገልጸው፥ “ይህም የተጠመቁ ሰዎች የመሆን ጥሪያችን ነው” ሲሉ ለቅዱስ እንድርያስ የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት አባላት በድጋሚ ተናግረዋል። “ሁላችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ እንሆን ዘንድ የተቀበልነውን ልናስተላልፍ ይገባናል” ሲሉ አክለዋል።

ፍሬያማ ሥራ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከአባላቱ ጋር በነበራቸው ጊዜ ማጠቃለያ ላይ፥ የቅዱስ እንድሪያን የስብከተ ወንጌል ትምህርት ቤት አባላት በእነዚህ የንግደት ቀናት ውስጥ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በመሰሉ ታማኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ቅዱሳን ሕይወት ላይ በማሰላሰል መልካም ቃሎቻቸውን እና ተግባሮቻቸው በተጨባጭ እንዲገልጹ ጋብዘዋቸዋል። በመቀጠልም ለሚያከናውኗቸው ፍሬያማ ሥራዎች ምስጋናቸውን አቅርበው፥ “በአዲስ ተስፋ መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ በማበረታታት፥ የወንጌል ተልዕኮአቸውን እንድትጠብቅ ለጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ማርያም አደራ ሰጥተዋል።

በመላው ዓለም ተሰራጭቶ የሚገኝ ትምህርት ቤት

በትምህርት ቤቱ ድረ-ገጹ ላይ እንደተገለጸው፥ የቅዱስ እንድሪያስ የወንጌል ትምህርት ቤት ዓለም አቀፍ ዋና መቀመጫ በሜክሲኮ ጓዳላጃራ የሚገኝ ሲሆን፥ ብሔራዊ ቅርንጫፎቹ በኮሎምቢያ፣ በጣሊያን፣ በብራዚል፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በሃንጋሪ፣ በፖርቱጋል፣ በካናዳ እና በአርጀንቲና ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1980 ዓ. ም. በሆሴ ፕራዶ ፍሎሬስ እና በአባ ኤሚሊያኖ ታርዲፍ በሜክሲኮ የተመሠረተው የወንጌል ትምህርት ቤት ዛሬ ወደ 69 በሚደርሱ አገራት ውስጥ እንደሚገኝ እና ወደ 2,000 የሚጠጉ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች እንዳሉት ታውቋል።

30 Aug 2025, 14:13