በካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ የሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጋ ጊዜ መኖሪያ ሥነ-ጥበብ እና ታሪክ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኡርባኖስ ስምንተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 10/1626 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ የበጋ ጊዜን በዕረፍት ያሳለፉ የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው። በግምት ከሮም በ25 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ይህች ከተማ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በበጋው ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 13/2017 ዓ. ም. ድረስ የዕረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው።
በጥንታዊ የሮማውያን ቪላ ፍርስራሽ ላይ የተገነባ
በካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ውስጥ በጥንታዊ የሮማውያን ቪላ ፍርስራሽ ላይ የተገነቡት ጳጳሳዊ ቪላዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ81-96 ዓ. ም. በነገሡት ሮማዊ ንጉሠ ነገሥት ዶሚቲያን ስም የሚጠሩት ናቸው።
በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በጋንዶልፊ ቤተሰብ የመኖሪያ ቪላ ፍርስራሽ ላይ የተገነባው ሕንጻው ለንጉሣዊ ቤተሰቦች ሲተላለፍ ቆይቶ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1596 ዓ. ም. ንጉሣዊ ቤተሰብ ለነበረው የሳቬሊ ቤተሰብ ተላልፏል።
በመጨረሻም ሐዋርያዊ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት ንብረቱን ከሳቬሊ ንጉሣዊ ቤተሰብ ተረክቦ እንደ ጎርጎርሳውያኑ ከ 1604 ዓ. ም. ጀምሮ የካስቴል ጋንዶልፎ ቪላዎች በቅድስት መንበር ንብረት ውስጥ ተካቷል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጋ ወቅት ማረፊያ ሥፍራ ታሪክ
በቀድሞው ስማቸው ማፌዎ ቪንቼንሶ ባርቤሪኒ የሚባሉት እና በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኡርባኖስ ስምንተኛ ተብለው የተጠሩት ጥንታዊ ቪላውን ወደ በጋ ጊዜ መኖሪያነት ቀይረውታል።
ባለፉት ዘመናት ውስጥ በካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ የሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣ ሲሆን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አሌክሳንደር ሰባተኛ በታዋቂው ጣሊያናዊ የሥነ-ሕንጻ ባለሞያ ቤርኒኒ ዕርዳታ ተጨማሪ ሕንጻዎችን አስገነቡ። እንደዚሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቄለሜንጦስ 14ኛ በአቅራቢያው የሚገኘውን ቪላ የገዙት ሲሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ አምስተኛ ቪላዎቹ እንዲታደሱ አድርገዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ሥፍራ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1870 ዓ. ም. የተከሰተውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳዊ መንግሥታዊ አስተዳደር ውድቀት ተከትሎ ለ 60 ዓመታት ገደማ ምንም ዓይነት አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቷል።
የቫቲካን የአትክልት ቦታዎች አስተዳደር
እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 1929 ዓ. ም. በቅድስት መንበር እና በጣሊያን መንግሥት መካከል ከተደረገው የላቴራን ስምምነት በኋላ የካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ አገልግሎት መስጠትን ቀጥሏል። የእድሳት ሥራዎች ከተከናወኑ በኋላ ሦስቱ ዋና ዋና ሰፋፊ የአትክልት ሥፍራዎች ማለትም ጃርዲኖ ዴ ሞሮ ወይም የሙር የአትክልት ሥፍራ፣ ቪላ ሳይቦ እና ቪላ ባርቤሪኒ እርስ በእርስ እንዲገናኙ ተደርጓል።
የአትክልት ሥፍራዎች እና ቫቲካን የሥነ-ከዋከብት ምርምር
የቫቲካን የሥነ-ከዋከብት ምርምር ማዕከል በሮም አቅራቢያ ያለው የብርሃን ብክለት ከፍተኛ በመሆኑ የምርምር ማዕከሉን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1934 ዓ. ም. ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ በማዛወት የኢየሱሳውያን ማኅበር አባቶች እንዲያስተዳድሩት በአደራ ተሰጥቷቸዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ፥ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2013 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ቫቲካን ውስጥ ወደሚገኘው ማተር ኤክሌሲያ ገዳም ከመዛወራቸው በፊት ባሉት ሳምንታት ውስጥ በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ውስጥ የኖሩት የመጨረሻው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ነበሩ።
ለዘመናት ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ታማኝ ሆነው የቆዩት የካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ነዋሪዎች በዘንድሮው የበጋ ወቅት የተወሰነ የዕርፍት ጊዜን ለማሳለፍ ወደ ሥፍራው የሚመጡትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛውን ለመቀበል በመዘጋጀት ላይ ይገኛሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለሐዋርያዊ የቤተ ክርስቲያን መሪነት ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ ሥፍራውን ለሁለት ጊዜ የጎበኙት ሲሆን፥ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ግንቦት 21/2017 ዓ. ም. በሥፍራው የታነጸውን “የውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር እና ሐዋርያዊ ሕንጻን በጎበኙበት ወቅት ሲሆን፥ ቀጥለውም ሰኔ 26/2017 ዓ. ም. በቪላ ባርቤሪኒ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉትን ሥራዎች ለመመልከት በተመለሱ ጊዜ እንደ ነበር ታውቋል።
በሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ የመጀመሪያ ወለል ላይ የሚገኘው የውሃ ውስጥ ነፍሳት መጎብኛ ሥፍራ ለሕዝብ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ የተነገረ ሲሆን፥ ቦታው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1841 እና 1931 መካከል የተገኙትን የአርኪኦሎጂ ቅርሶች የያዘ የሙዚዬሙ አካል እንደ ሆነ ታውቋል። ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትዕዛዝ ለሕዝብ ክፍት መደረጉ ይታውሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሥፍራው ያደረጓቸው ጉብኝቶች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መኖሪያ ውስጥ አንድ ሌሊት ሳያድሩ የካስቴል ጋንዶልፎ ከተማን ሦስት ጊዜ መጎብኘታቸው ይታወሳል። የመጀመሪያው ጉብኝታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በነበሩበት ወቅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 23/2013 እንደ ነበር ይታወሳል። ሥፍራው የተቀናጀ ልማትን ለማሳደግ እና የአካባቢ እንከባከቤን ለማሳደግ ይሚረዱ ትምህርታዊ እና ማኅበራዊ ሥራዎችን ለማካሄድ የታሰበ እንደሆነ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሚያርፉበት ቦታ
ከቀደምቶቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በተለየ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሚያርፉት በሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ሳይሆነ ነገር ግን በስፋቱ እስከ ዛሬ ድረስ በዋነኛነት እንደ መናፈሻ በሚያገለግለው በቪላ ባርቤሪኒ ሕንጻ ውስጥ እንደሚሆን ታውቋል።
ሕንጻው አስቀድሞ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሞምፔኪዮ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሺፒዮኔ ቪስኮንቲ የተገነባ ትንሽ ቤተ መንግሥት ነበር።
ቆይቶም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1630 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኡርባኖስ ስምንተኛ የወንድም ልጅ በሆነው በታዴዎ ባርበሪኒ የተገዛ ሲሆን፥ የአትክልት ሥፍራውን በወይራ ዛፎች፣ በአትክልት ሥፍራዎች፣ በአጥር እና በድንጋይ በተሸፈነው የእግረኛ መንገዶች ተስፋፍቷል።
ሙዚየሙ አሁንም ለሕዝብ ክፍት ነው
የሙዚዬሙ ጉብኝቶች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ አሥራ አራተኛ በሚቆዩባቸው ቀናትም ለሕዝብ ክፍት ሆነው ይቆያሉ። እንደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ሕዝባዊ ዝግጅቶች እና በተለይም በእሁድ ቀናት በሚያቀርቧቸው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት ሊደረጉ የታቀዱ አንዳንድ ለውጦች ቢኖሩም ምእመናን በአቅራቢያው በሚገኘው የነፃነት አደባባይ ይሰበሰባሉ።
ከሙር እና ከሚስጥር የአትክልት ሥፍራዎች በተጨማሪ ጎብኚዎች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የግል ሕይወት በሚያሳዩ፥ በልማድ ተዘግተው በሚቆዩ አካባቢዎች ጉብኝቶችን ማድረግ ይችላሉ። ከከተማ ስምንተኛ ትንሽ የጸሎት ቤት እስከ ቢሊያርድ ክፍል እና የሙዚቃ ክፍል። ነገር ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሚቆዩባቸው ቀናት ውስጥ የቫቲካን የሥነ-ከዋከብት ምርምር ማዕከል ለጉብኝት ክፍት ሆኖ ይቆያል።
ሰዎች የሚጎበኟቸው ቦታዎች
የሙዚዬሙ ዋና አካል ሐዋርያዊ ሕንጻ ሲሆን፥ የመግቢያ ትኬቶችን ከቲኬት ቢሮ ወይም ከቫቲካን ሙዚዬሞች ድረ-ገጽ ላይ መግዛት ይቻላል። በቲኬቶቹ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቁም ሥዕሎች የያዘውን እና በመጀመሪያው ፎቅ ላይ የሚገኘውን ጋለሪ መጎብኘት የሚቻል ሲሆን፥ እንዲሁም በሁለተኛው ፎቅ ላይ የሚገኘውን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይቆዩ የነበሩበትን ክፍል የሚያካትት ሐዋርያዊ ሕንጻን መጎብኘት እንደሚቻል ታውቋል።
እነዚህም የካርዲናሎች መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ዙፋን የሚገኝበት ክፍል፣ የስዊስ ዘብ ክፍል፣ የመኝታ ክፍል፣ የግል ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መጻሕፍት እና የጥናት ክፍልን ያካትታሉ። እነዚህ ቦታዎች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ ተባባሪዎች ብቻ ይጎበኙ እንደ ነበር ታውቋል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መሸሸጊያ የነበሩ ቦታዎች
የሙዚዬሙ ሕንጻ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር ወር 2024 ዓ. ም. የተመረቁትን የታሪክ ስብስቦችን እና አዳዲስ የኤግዚቢሽን ቦታዎችንም ያካትታል።
የመግቢያ ቲኬቱ ሦስት ኤግዚቢሽኖችን የሚያካተት ሲሆን፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማትን፣ በሠዓሊ ራፋኤል የተዘጋጀው የቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ መውገርን እና ካስቴል ጋንዶልፎ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1944 ዓ. ም. ምን ይመስል እንደ ነበር የሚያሳይ ኤግዚቢሽኖች ያሉባቸው ክፍሎች ናቸው።
የመጨረሻው ኤግዚቢሽን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ሥፍራ ውጭ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ትእዛዝ፥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የቦምብ ጥቃትን ሸሽተው የመጡ ከ12,000 በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች መሸሸጊያን ያገኙባቸውን ወራት የሚያስታውስ ነው።
በእነዚያ ወራት ውስጥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አልጋ ላይ ወደ 40 የሚጠጉ ልጆች የተወለዱ ሲሆን፥ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ መንታ ልጆች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ክብር ሲባል ዩጂኒዮ ፒዮ እና ፒዮ ዩጄኒዮ የሚል ስም እንደተሰጣቸው ይታወሳል።